በእስራኤል እና ኢራን ግጭት ሁለቱም ሀገራት ሚሳኤሎችን ማስወንጨፋቸውን እንደቀጠሉ ናቸው

የእስራኤል እና ኢራን ግጭት ሁለቱም ሀገራት ሚሳኤሎችን ማስወንጨፋቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግጭት አውዳሚውን የኒውክሌር ጦርነት እንዳያስጀምረውም ተሰግቷል፡፡ ይህንን የሰጉ ሀገራት ግጭቱ በቶሎ እንዲቋጭ ሲጠይቁ እንደ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ያሉ ሰዎች ደግሞ ሀገራት አንዳንዴ መፋላም አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል የኢራኑን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒን ለመግዳል የነበራትን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸው እየተሰማ ነው፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በያዘችበት ዓለም መኖር አንችልም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ይህንን ስል ግን እስራኤል ኢራን ላይ ባደረሰችው ጥቃት የፈረንሳይ እጅ አለበት ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ኢራን በቀጠናው ትርምስ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላት አውቃለሁ ነው ያሉት፡፡

የእስራኤል ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት እንዳስታወቀው ኢራን በማዕከላዊ እስራኤል ትናንት ሌሊት በፈጸመችው ጥቃት አምስት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል፡፡

እሁድ ዕለት እስራኤል በቴህራን በፈጸመችው ጥቃት የኢራን ጦር ሃይሎች የስለላ ክፍል ኃላፊ ገድላለች፡፡

በቴል አቪቭ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢራን ጥቃት መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰበትም ተሰምቷል፡፡

እሁድ ምሽት ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በቴል አቪቭ በሚገኘው  የኤምባሲያቸው ቅርንጫፍ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደር ማይክ ሃካቢ በኤክስ ገጻቸወ ላይ ቆንስላው ከኢራን በተወነጨፉ ሚሳኤሎች ንዝረት ሳቢያ ጉዳት ስለደረሰበት ዝግ ሆኖ ይቆያል ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ በቴል አቪቭ እና በእየሩሳሌም የሚገኙ ሠራተኞቹ በመጠለያ ውስጥ እንዲቆዩ ካሳሰበ በኋላ ነው ይህ ጥቃት መድረሱ የተሰማው፡፡

ከእስራኤል ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ለቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት እንደሚቀጥል እና መጠኑም  ሊሰፋ እንደሚችል የኢራን ገላጋይ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

የእስራኤል ጦር በኢራን የኪድስ ኃይል የጦር ማዘዣ ማዕከልን እንዲሁም የሚሳኤል ማስወንጨፊያን ከነተቆጣጣሪ ወታደሮቹ ጋር መምታቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ የቀጠለውን ጥቃት በጋራ ለመመከት የኢራን ህዝብ አንድነት እንዲጠናከር ጥሪ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡

ኢራን በእስራኤል ላይ ባደረሰችው ጥቃት እስካሁን አራት ሰዎች መሞታቸው ሲነገር፤ወደ 87 የሚደርሱ ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን መረጃዎች እያመላከቱ ነው፡፡

በእስራኤል ጥቃት ኢራን ውስጥ ከ220 በላይ ሰዎች ሲገደሉ 1ሺ500 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የኢራን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢራን ሁለት የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ ባልደረቦችን በቴህራን አቅራቢያ በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብላለች፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናሁ እስራኤል የኢራንን ስጋት ለማስወገድ ቆርጣ ተነስታለች ሲሉ መናገራቸው ተደምጧል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe