በእነ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ተካተው በእስር ላይ የነበሩ ግለሰቦች ከእስር እንዲፈቱ ታዘዘ!

የቀድሞ የደህንነት ቢሮ ዳይሬክተር በነበሩት በእነ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ተካተው ከ3 ዓመት በላይ በእስር ላይ የነበሩ ግለሰቦች ከእስር እንዲፈቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ አስተላለፈ።አዲሱ በዳሳ፣ ሳሙኤል ጊዲሳና ደርሶ አየነው የተባሉ ተከሳሾች በትናንትናው ዕለት በፍርድ ቤት ከተወሰነባቸው የቅጣት ውሳኔ በላይ በእስር በማሳለፋቸው (የእስር ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው) ነው ከእስር እንዲፈቱ የታዘዘው።

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ከተከሰሱት በእነ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ተካተው የነበሩት 17ኛ ተከሳሽ አዲሱ በዳሳ 18ኛ ሳሙኤል ጊዲሳ እና 24ኛ ተከሳሽ ደርሶ አየነው ከጥቅምት ወር 2011 ጀምሮ በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።እነዚሁ ሦስቱ ተከሳሾች በየካቲት 25 ቀን 2014 በነበረ የችሎት ቀጠሮ “ባልሰራንበት ወንጀል አራት ዓመት ታስረናል፤ የተፋጠነ ፍትህ ለማግኘት እንድንችል የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ አንፈልግም።” በማለት ጉዳያቸው ተነጥሎ ፍርድ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበረም ይታወሳል።

በተለይም 24ኛ ተከሳሽ ደርሶ አየነው ያለጥፋቱ አራት ዓመት መታሰሩን ጠቅሶ በእያንዳንዷ ቀናት ቤተሰቦቹ ከቀለብ ጀምሮ መቸገራቸውን ገልጾ ነበር።ፍርድ ቤቱ የፈለገውን ፍርድ ይፍረድብን እና እንረፍ ሲሉ የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በዚሁ የካቲት 25 ቀን 17ኛና 18ኛ ተከሳሽ የነበሩት አዲሱና ሳሙኤል የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አያይዘው በጽሁፍ አቅርበው ነበር።ፍርድ ቤቱም ከክስ መዝገቡን የሦስቱን ተከሳሾች ጉዳይ ነጥሎ መርምሯል።

በዚህም ተከሳሾቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውና ለአገር ልማት ያደረጉትን አስተዋጾ አክለው ያቀረቡትን 5 የቅጣት ማቅለያ ፍርድ ቤቱ ይዞላቸዋል።በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ትላንት ከሰዓት በኋላ በዋለው የችሎት ቀጠሮ፤ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ በተባሉበት አንቀጽ አዱሱ በዳሳና ሳሙኤል ጊዲሳን እያንዳንዳቸውን የ3 ዓመት እስራትና የ3 ሺህ 500 ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፤ 24ኛ ተከሳሽ ደርሶ አየነውን በተመለከተ ደግሞ በኹለት ዓመት እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም መሰረት አዲሱ በዳሳና ደርሶ አየነው ከታሰሩበት ከጥቅምት ወር 2011 ጀምሮ ታሳቢ ሲደረግ፤ ከቅጣቱ በላይ በመታሰራቸውና የእስር ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው ከትላንት ጀምሮ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ መሰጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።ሳሙኤል ጊዲሳን በተመለከተም እስካሁን የታሰረበት ጊዜ በመዝገቡ ላይ ያልተካተተ ቢሆንም፤ የታሰረበት የጊዜ መጠን ተጣርቶ በተመሳሳይ ከእስር የሚፈታ ይሆናል ተብሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe