በሁቲዎች እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ከ2,000 በላይ ሰዎች ከየመን ወደ ጅቡቲ መሰደዳቸዉ ተገለጸ፡፡
በየመን ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት እስከ አሁን ድረስ 85 ሽህ 818 ሰዎችን እንዳፈናቀለ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኤም.ኦ) ገልጿል።
የጅቡቲ ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ኢልያስ ኤም ዳዋሌህ በበኩላቸው በ24 ሰዓት ውስጥ 1,400 የየመን ዜጎች ጅቡቲ እንደደረሱ የገለጹ ሲሆን የዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጀት ደግም አሁን ላይ ቁጥሩ ከ2,000 ማለፋቸዉን አመላክቷል፡፡
ሚንስትሩ ባጋሩት የጽሑፍ መረጃ 500 ሴቶችንና ህጻናት ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች በባብ ኤል መንደብ የባህር ወሽመጥን ሲያቋርጡ ነዳጅ መጨረሳቸዉን ተከትሎ በባህር ላይ እርዳታ እንደተደረገላቸው ገልጾ ወደ ኦቦክ የባህር ዳርቻ ከተማ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ኦቦክ ከየመን የባህር ዳርቻ መንገድ 20 ኪሎ ሜትር ብቻ የምትርቅ ከተማ ስትሆን ለበርካታ ዓመታት በጦርነት ከተጎዳችዉ የመንን ለቀዉ የሚሰደዱ የመናውያን ተመራጭ የመግቢያ ቦታ ሆናለች።
የዓለም አቀፉ የፍልተሰኞች ድርጅት የሰብአዊ ምላሽ አስተባባሪ ሳፊያ ኢብራሂም “እንደ ሴቶችና ህጻናት ያሉ ተጋላጭ ማህበረሰቦች የኦቦክ የባህር ዳርቻ ደርሰዋል፡፡ በሚቀጥሉት ቀናትም ተጨማሪዎች ይጠበቃሉ” ብለዋል፡፡
ጅቡቲ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ስታስተናግድ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ እ.ኤ.አ. መጋቢት 2026 የወጣው አሃዝ እንደሚያመላክተዉ ከሆነ የተመዘገበው የፍልሰተኞች ቁጥር ከ36,000 በላይ ሲሆን አብዛኞቹ ከሶማሊያ፣ ከኢትዮጵያና ከየመን የመጡ ናቸው።
ሁቲዎች ባለፈው ሐሙስ ዕለት በቀይ ባህር ዳርቻ የሚገኘውን የሞካ ከተማ በመቆጣጥተር ከዚያም በባብ ኤል-መንደብ የባህር ወሽመጥ ዙሪያ ያለውን የባህር ዳርቻና ደሴቶች ሲቆጣጠሩ በፈፀሙት ጥቃት በሽዎች የሚቆጠሩ አካባቢያቸውን ለቀው ተሰደዋል።

