” በደም ግፊት የሚመጣ ሞት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ” – ዶክተር አምደመስቀል መርሻ በኢትዮጵያ በደም ግፊት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች ገዳይ የበሽታ አይነቶች በላቀ መልኩ እየጨመረ ነው። የየካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር አምደመስቀል መርሻ ” በኢትዮጵያ የደም ግፊት በሽታ ተጠቂች መጠን ከዚህ ቀደም ከነበረበት ወደ 17.3% ጨምሯል ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል። ” ህክምናው፣ እድገቱ በአንጻራዊነት እየሰፋ በመምጣቱ ገዳይ በሚባሉ እንደ ኤችአይቪ ኤድስ፣ ወባ፣ ቲቢ፣ በማስቀመጥና ከአንገት በላይ በሽታ፣ በመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን ባሉ ህመሞች ሚመጣው ሞት እየቀነሰ ሲመጣ፣ የደም ግፊት ግን እየጨመረ መጥቷል ” ሲሉ ገልጸዋል። የእነዚህ የተዘረዘሩት በሽታ አይነቶች ዓመታዊ የሞት መጠን ቢደመር 8 ሚሊዮን ሲሆን፣ የደም ግፊት ብቻ ግን 10.5 ሚሊዮን መሆኑን አስረድተዋል። በደም ግፊት የሚመጣ ሞት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
” የደም ግፊትን በደንብ ካልተቆጣጠርነው በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ። አሁን ባለው ዳታ መሰረት 10 ሚሊዮን ህዝብ በደም ግፊት ህይወቱን ያጣል። ግን ያ ሁሉ በደንብ ከታከመና ግፊቱን መቆጣጠር ከተቻለ ይሄ ሁሉ ሞት መቀነስ የምንችለው ነው ” ብለዋል። ግፊት በራሱ ከሚያስከትለው ሞት ባሻገር ከግፊት ጋር ተያይዘው የሚመጡ እንደ ስትሮክ አይነትም በሽታዎች ለሞት እንደሚዳርጉ አስረድተዋል። ” ብዙዎቹ እነዚህ መሰል ሞቶች ማስወገድ፣ መቀነስ የምንችላቸው ቢሆኑን ማህበረሰቡ ወደ ህክምና የመሄድ ልምዱ ዝቅተኛ ነው ” ብለዋል።
የግፊት በሽታ መኖሩ የሚታወቀው ውስጥ ለውስጥ ጉዳት ካደረሰ በኋላ አንድ የሰውነት ክፍል በመጠቃቱ በሚታዩ ምልክቶች፣ አንዳንዴም ህይወት ካለፈ በኋላ መሆኑን ገልጸው፣ በየጊዜው የግፊት መጠንን በህክምና መከታተል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በዓለም የጤና ድርጅት ጥናት መሰረት በዓለም ላይ በእያንዳንዷ ሰዓት 1,000 ሰዎች በግፊት ህይወታቸው እንዲሚያልፍ፣ አዋቂ ከሆኑ ከሦስት ሰዎች ውስጥ አንዱ የደም ግፊት እንዳለበት ገልጸው፣ ነገር ግን ” በሚያሳዝን ሁኔታ ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ የግፊት በሽታ እንዳለባቸው አያውቁም ” ብለዋል። ለግፊት አጋላጭ ምልክቶች ምንድን ናቸው ? ዶ/ር አምደወርቅ፣ ለደም ግፊት አጋላጭ ምክንያቶች ብዙ ጊዜ እንደማይታወቁ ሲገልጹ፣ ” ከ90% በላይ የሚሆነው የግፊት መንስኤ ብዙ ምርመራዎች ተደርገውም አይታወቅም። ስለዚህ ያለው አማራጭ ግፊትን በመድኃኒት መቆጣጠር ነው ” ሲሉም ተናግረዋል። በተያያዘ፣ ምንም እንኳ እንደ ፦
- ውፍረት
- እንቅርት
- የደም ቧንቧ ችግር
- ያለአግባብ መድኃኒት መውሰድ እና መሰል ጉዳዮች የግፊት መንስኤዎች ቢሆኑም፣ ምልክቶቹ የሚታዩት በሽታው ከጎዳ በኋላ መሆኑን በመግለጽ፣ ብዙ ጊዜ የደም ግፊት ምልክት የለውም። የግፊት ህክምና የሚያስፈልገው እነዚህን ችግሮች ለመከላከል ነው ብለዋል። ግፊትን የሚያፋጥኑ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ?
- ጨው የበዛበት ምግብ መመገብ፣
- አትክልትና ፍራፍሬ አለመመገብ፣
- አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድግ፣
- የአልኮል መጠጦች፣
- ሲጋራ ማጨስ፣
- የሰውነት ክብደት መጨመር፣
- በቤተሰብ የዘር ሀረግ መወራረስ እና የመሳሰሉት መሆናቸውን ገልጸዋል። ቁጥሮች ምን ይላሉ? በዓለም ጤና ድርጅት ጥናት መሰረት በዓለም ላይ ካለው ጠቅላላ 8 ቢሊዮን ህዝብ 1.4 ቢሊዮን የሚሆኑት የደም ግፊት አለባቸው። ከእነዚህ ውስጥ ግፊቱ እንዳለባቸው የሚያውቁት 800 ሚሊዮን ሲሆኑ፣ 600 ሚሊዮን ደግሞ በሽታው እንዳለባቸው አያውቁም። የደምግፊት እንዳለባቸው ከሚያውቁት 800 ሚሊዮን የዓለም ህዝቦች 160 ሚሊዮን የሚሆኑት አውቀውም ህክምና ማድረግ አይጀምሩም። ከ800 ሚሊዮኖቹ መካከል 630 ሚሊዮኑ ደግሞ ህክምና ቢጀምሩም በስርዓቱ ተከታትለው ግፊታቸውን የሚቆጣጠሩት 320 ሚሊዮን ብቻ ናቸው። የደምግፊት በሽታ የሰዎችን ህይወት ከመቅጠፉ ባሻገር፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ በዓመት ወደ ለ3.7 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ወጭ እንደሚያስደርግ ጥናቶች ያሳያሉ።
- ቲክቫህ ኢትዮጵያ

