የፊንቴክ ተጠርጣሪዎች ለሚያዝያ 28 ተቀጠሩ
በ’ፊንቴክ ኢንቨስትመንት’ የማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች ላይ አቃቢ ህግ ክስ መስርቶ እንዲያቀርብ ሰባት ቀናት ተፈቀደለት።
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፥ በ’ፊንቴክ ኢንቨስትመንት’ የማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች ላይ መርማሪ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ እንዲያቀርብ ለዛሬ ሚያዚያ 21/2018 ዓም ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።
በቀጠሮው መሰረት የተሰየመው ችሎቱ ሚያዝያ 9/2018 ዓም በተሰየመበት ወቅት መርማሪ ፖሊስ ጠይቆት ከነበረው የተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ ችሎቱ “ፖሊስ የመጨረሻ የምርመራ መዝገቡን አደራጅቶ እንዲያቀርብ በሚል” በሰጠው የሰባት ቀናት ጊዜ መሰረት በፖሊስ በኩል የተጠናቀረውን የምርመራ መዝገብ በዛሬው ዕለት አድምጧል።
መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ የክስ መዘገቡን አደራጅቶ ለአቃቢ ህግ ማቅረቡን ገልጿል።
በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከ 7 ሺ ገጾች በላይ የክስ መዝገብ መደራጀቱን የገለጸው አቃቢ ህግ በመዝገቡ ላይ 1ሺ 400 ተበዳዮች መኖራቸውን ከእነዚህ ተበዳዮችም ፖሊስ የ150ውን ቃል መቀበሉን ፣ ከ 12 ሚዲያዎች፣ከ 15 ባንኮች ደግሞ በተጠርጣሪዎች ዙሪያ ያሉትን መረጃዎችን መሰብሰቡን በዝርዝር አስረድቷል።
ስለሆነም ያለውን የማስረጃ ብዛት፣ የተበዳዮችን ብዛት፣ እና የጉዳዩን ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባት መዝገቡ ሊያስከትል የሚችለው ተደራራቢ ክስ የመመስረቻ የ 10 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን ሲል አቃቢ ህግ ችሎቱን ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው “ተጠርጣሪዎቹ ማህበራዊ መሰረት ያላቸው፣ የጤና እክል ያለባቸው እንዲሁም በተፈለጉበት ጊዜ ሊመጡ የሚችሉ መሆናቸውን በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ተከራክረዋል።
በተጨማሪም የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ለአቃቢ ህግ መቅረቡን በመግለጽ አቃቢ ህግ ክሱን እስኪመሰርት ደንበኞቻችን በእስር መቆየት የለባቸውም በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ አቃቢ ህግ ለክስ መመስረቻ ከጠየቀው የ 10 ቀናት ጊዜ ውስጥ ሰባቱን ቀናት በመፍቀድ ክስ መስርቶ እንዲያቀርብ ለሚያዝያ 28/2018 ዓ/ም ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።

