በፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሰረት ያለተመዘገቡ መመሪያዎች ህጋዊ መሠረት የላቸዉም ተባለ::የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራትና አጠቃላይ ሂደቶች ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫዉን የሰጡት የሕግ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዳባ ሲሆኑ በመግለጫቸውም ከለውጡ በኻላ ከሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጋር በተያያዘ በርካታ አዋጆችን የማሻሻልና አዳዲስ አዋጆችን የማውጣት ተግባራት አከናውነናል ለአብነት ያህልም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የጸረ-ሽብርና ሌሎች በርካታ አዋጆችን የማሻሻል እንዲሁም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ዉስጥ በማስገባት የእርቀ ሰላም ኮሚሽንና የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጆችን የማውጣትና ተግባራዊ እንዲደረጉ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከ60 ዓመታት በላይ የስቆጠሩ ህጎችን የማሻሻል ስራ የተሰራ ሲሆን በቀጣይነትም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ከተሰሩ ስራዎች መሃከል ለአብነት ያህል የንግድ ህግን የማሻሻል ሥራው ተጠናቆ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ የተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉም የማሻሻያ ስራዉ ተጠናቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ በመሆኑ በቅርቡ በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅራቢነት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በፌደራል መንግስት እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየው በተለይም ከመመሪያዎች ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑ የተጠቀስ ሲሆን ህግ የማውጣ ስልጣን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሆንም የፌደራል ተቋማትና ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የየራሳቸዉን የአሰራር መመሪያ የማዉጣት ውክልና ተሰጥቷቸዋል ነገር አንዳንድ ተቋማት የተሰጣቸውን የውክልና ሥልጣን ባልተገባ መልኩ በመጠቀም ህጋዊ መሰረት የሌላቸውንና የተገልጋዩን ማህበረሰብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥሱ መመሪያዎችን አውጥተው ሰጠቀሙ ይስተዋላል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፡፡
አቶ ተስፋዬ አክለዉም በሕግ መንግሰቱ ዉስጥ የመንግስት ሥራ ግልጽና ተጠያቂነት ባለው መልኩ መመራት አለበት ተብሎ ግልጽ ሆኖ የተቀመጥ ቢሆንም አንዳንድ አስፈጻሚ ተቋማት ግን ህጋዊ መሰረት የሌላቸውንና አሳታፊ ያልሆኑ መመሪያዎችን በሚፈልጉበት መንገድ በማዉጣት ተገልጋዩን ማህበረሰብ ለከፋ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲዳርጉ ቆይተዋል ይህንን ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከመጋቢት 29/2012 ዓ.ም ጀምሮ የፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 እንዲጸድቅ ሲደረግ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች ከተቋማቱ የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ይችሉ ዘንድ የሚወጡ መመሪያዎች በጠቅላላ ግልጽነት ያላቸው እንዲሁም ተገልጋዩን ማህበረሰብ አሳታፊ ያደረጉና ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሁም በፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሰረት የተመዘገቡና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና መመሪያዉን ባወጣዉ ተቋም ደረ-ገጽ ላይ ተጭኖ ለህብረተሰቡ ይፋ የተደረገ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የአዲሰ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር መ/ቤቶችን ጨምሮ በፌደራል አስፈጻሚ ተቋማት እስከ አሁን ድረስ በአዋጁ መሰረት የተመዘገቡ መሪያዎች ብዛት 857 ብቻ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ለአብነት ያህል የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር 66፣ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ 159፣ ገንዘብ ሚኒስቴር መ/ቤትና ተጠሪ ተቋማቱ 89፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒሰቴር መ/ቤት 73 እንዲሁም ለሎች ተቋማትም በተዋረድ ያወጡትን መመሪያዎች እያስመዘገቡ ሲሆን በተቃራኒው የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ግን ምንም አይነት መመሪያ አላስመዘገበም ተብሏል፡፡
የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ያወጡጥን መመሪያዎች ያላስመዘገቡ ተቋማት በሥራ ላይ ያዋሉት መመሪያዎች ህጋዊ መሰረትና ተፈጻሚነት እንደሌላቸው ተረድተው በአዋጁ መሰረት እንዲያስመዘግቡና ህገ መንግስታዊ ግዴታቸዉን እንዲያከብሩ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን ያልተመዘገቡና ተፈጻሚነት የሌላቸውን መመሪያዎች ተጠቅመው መንግስታዊ ስራዎችን እያከናወኑ ያሉና ከዚህ የተነሳ ባልተገባ መልኩ በተገልጋዩ ማህበረሰብ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ ተቋማት ስያጋጥሙ በፍርድ ቤት በኩል ክስ በመመስረት የተወሰነባቸውን ውሳኔ ውድቅ የማስደረግና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸዉን የማስጠበቅ መብት እንዳላቸው በጋዜጣዊ መግለጫዉ ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም ተቋማቱ በአዋጁ በተቀመጠው አግባብ መሰረት ያሏቸውን መመሪያዎች በሙሉ በማስመዘገብና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና በየራሳቸው ድረ-ገጾች በመጫን ተደራሽ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ የማስገንዘብ ብሎም ይህንኑ እንዲያደርጉ ደብዳቤ የመጻፍ ሥራ ቢሰራም ምላሽ የሰጡ ተቋማት አነስተኛ መሆናቸው ታይቷል በመሆኑም ተቋማቱ አሁንም ቢሆን ህገ-መንግስታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አቶ ተስፋዬ ዳባ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡

