• የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ብር 46.39 ቢሊዮን ደርሷል፡፡
• ለልማትና በጎ አድራጎት ተግባራት የ41.8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ቡና ባንክ አ.ማ ዓመታዊውን የባለአክሲዮኖች 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እሁድ ሕዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም አካሂዷል።
በአዲስ ፓርክ ሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደውና በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች በታደሙበት በዚሁ ጉባዔ ላይ የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ የባንኩን የ2022/23 ዓመታዊ ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች በንባብ አቅርበዋል።
ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከግብር በፊት 1.35 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ከ36 ነጥብ 59 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ ችሏል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ ይፋ እንደተደረገው ባንኩ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2023 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ9.4 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የቻለ ሲሆን በዚህም የባንኩን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ34.6 በመቶ ከፍ በማድረግ 36.6 ቢሊዮን ብር እንዳደረሰው ተነግሯል። ከዚህ ውስጥ የቁጠባ ሂሳብ ተቀማጭ 73.3 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ ይዟል።
አምባሳደር ዓለማየሁ በንግግራቸው እንዳሰመሩበት ከሆነ ቡና ባንክ በሀገራችን ላይ የተፈጠረው የሰላምና ጸጥታ ችግር እንዲሁም የውጪ ገንዘብ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ውስጥ ያለው ሰፊ የተመን ልዩነት በአገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደሩትን ጉልህ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን ተቋቁሞ አትራፊነቱን ማስቀጠልና በአጠቃላይ አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት በላቀ ደረጃ ላይ መገኘት ችሏል። ይህም ለባንኩ ባለአክሲዮኖችና ለአጠቃላይ ሰራተኞቹ የሚያበረታታ ውጤት ነው ብለዋል።
በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ባንኩ በዓመቱ ውስጥ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በአጠቃላይ 8.92 ቢሊዮን ብር አበድሯል። ይህም ቡና ባንክ በአጠቃላይ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያበደረውን የገንዘብ መጠን በ34.5 በመቶ በማሳደግ 34.78 ቢሊዮን ብር አድርሶታል።
ከውጭ ሃገር የሚላክ ሀዋላ ከላይ በተገለጹት ዓለምአቀፋዊና ሃገራዊ ችግሮች ባስከተሉት ተጽእኖ ሳቢያ መቀነሱ እንዲሁም የኤክስፖርት ስራ ጉልህ በሆነ መልኩ መቀዛቀዙ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል የባንኩን አፈፃፀም በታቀደው መልኩ እንዳይከናወን አሉታዊ ጫና አሳድሯል ያለው የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት በዓመቱ የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝት 175.7ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር መሆኑንም ጠቁሟል። ከዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ 55.5 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ቀዳሚ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
ባንኩ የውጭ ሃገራት ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር የቀጥታ ግንኙት መስርቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ሪፖርቱ አብራርቷል።
በቦርዱ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ ሪፖርት ውስጥ ከተካተተው አንዱ የባንኩን ጠቅላላ ሃብት የተመለከተ መረጃ ሲሆን እንደሪፖርቱ የባንኩ ጠቅላላ ሃብት በበጀት ዓመቱ የ12.29 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቶ 46.39 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ሊቀመንበሩ ባቀረቡት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንደተብራራው የባንኩ ካፒታል በበጀት ዓመቱ የብር 1.5 ቢሊየን ብር እድገት አሳይቷል። ይህም የባንኩን አጠቃላይ የካፒታል መጠን 6.5 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ቡና ባንክ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ብሎም የተቀማጭ ማሰባሰቡን ሥራ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል በበጀት ዓመቱ 122 አዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም ባንኩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የከፈታቸውን ቅርንጫፎች መጠን 465 አድርሶታል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምቹ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብና አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ በተደረገው እንቅስቃሴ ባንኩ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞቹን ቁጥር በ1ሚሊዮን 89ሺህ 400 ከፍ በማድረግ የ55.6 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉም ተብራርቷል። ይህም አፈጻጸም የባንኩን አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 3 ሚሊዮን 050 ሺ 253 ከፍ አድርጎታል።
የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎትን በተመለከተ በ2022/23 በጀት ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች፣ ሆቴሎች፣ እና የንግድ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ የተተከሉ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ቁጥር 194 ደርሷል።
በተመሳሳይም ሪፖርቱ እንደጠቆመው የአዳዲስ ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 170ሺ 824 ደርሷል፡፡ በዚህም የባንኩ አጠቃላይ የካርድ ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 371ሺ021 የደረሰ ሲሆን በባንኩ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች 1.8 ቢሊየን ብር ማንቀሳቀስ መቻሉም ተጠቁሟል።
በተያያዘ የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደጉን ፣ በዚህም በድምሩ 10.6 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ መደረጉን ሪፖርቱ ገልጻል፡፡
ቡና ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የራሱ ልዩ መለያ እና የንግድ ስም እንዲኖረው በማስቻል “ኻዲም” (KHADIM)” የተሰኘ የአገልግሎት መለያ በመያዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ስራ መስራት መቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ ይህም በባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተገኘውን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ብር 1.63ቢሊዮን አድርሶታል ተብሏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በደንበኞች የተከፈቱ 183ሺ632 አዳዲስ ከወለድ ነፃ ሂሳቦች አጠቃላይ የባንኩን የወለድ ነጻ ደንበኞች ቁጥር ወደ 295 ሺ 541 አድርሶታል ብሏል ሪፖርቱ።
ሪፖርቱ በዋናነት ካካተታቸው አብይ ተግባራት መካከል የባንኩን የማህበራዊ ሃላፊነት የተመለከተው ክፍል ይገኝበታል።
ቡና ባንክ በሃገር ግንባታ እንዲሁም የህዝብን ህይወት ለመለወጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመንግስት በሚካሄዱ ጥረቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለቀረበለት ጥሪ በሰጠው ምላሽ በበጀት ዓመቱ በድምሩ 41.8 ሚሊዮን ብር ለማህበራዊ ድጋፍ፣ ለአካባቢ ተኮር ፕሮጀክቶችና ለሌሎች ግብረ ሰናይ ተግባራት እንዲውል ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።
ይህ የባንኩ ሃገራዊ ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የቦርዱ ሊቀመንበር አምባሳደር አለማየሁ ሰውአገኝ አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ባንኩ ሀብቱን ከማሳደግ እና ገጽታውን ከመገንባት አንጻር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ሰንጋ ተራ በሚባለው አካባቢ በተረከበው 1043 ስኩየር ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ከምድር በታች 3 ወለል እና ከምድር በላይ 23 ወለል ሁለገብ ህንጻ ግንባታ ስራ ለማካሄድ ከግንባታ ስራ ተቋራጭ ጋር የስራ ውል መፈረሙን፣ ከዚህ በፊት በተለምዶ ዲ አፍሪክ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የህንጻ ግንባታ አገልግሎት የሚውል 4ሺ 530 ካሬ ሜትር መሬት በሊዝ ይዞታ የባለቤትነት መብት ለመረከብ የመጨረሻ ምእራፍ ላይ መድረሱን እና ለመጋዘን አገልግሎት የሚሆን ስፋቱ 1550 ካሬ ሜትር ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ፣ ንፋስ ስልክ አካባቢ መረከቡን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት አመልክቷል።
ከተመሰረተ 14 ዓመታት የሞላው ቡና ባንክ ከ13ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖችና ከ4ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉት። (ቡና ባንክ)

