(ቁም ነገር ሚዲያ ፤ታህሳስ 3፤2018)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተረጋግጦ የተመዘገበ የመሬት ይዞታ ባለመብት የሆነ ሰው የመሬት ይዞታ መብቱ ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ፤ በተከናወኑ ምዝገባዎች መሠረት በሚሰጡ የምዝገባ ማረጋገጫ ሰርተፊኬቶች ላይ ዋስትና በመስጠት ሕብረተሰቡ በመሬት ይዞታ ምዝገባ ስርዓት ላይ እምነት እንዲኖረው ማድረግ በማስፈለጉ፤ እንዲሁም በተሰጡ የምዝገባ ማረጋገጫ ማስረጃዎች መሠረት በማድረግ ሦስተኛ ወገኖች በቅን ልቦና በሚፈጽሙት ተግባር ምክንያት ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሣ ለመክፈል የሚያስችል የዋስትና ፈንድ ማቋቋም ስለአስፈለገ በሚል በኤጀንሲው በሚፈፀም የመሬት ይዞታ መብት የስም ዝውውር ላይ ተፈፃሚ የሚሆን አስገዳጅ ደንብ ማውጣቱ ታውቋል፡፡
ደንብ ቁጥር 108/2ዐ11 የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የዋስትና ፈንድ ማቋቋሚያ በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ሰሞኑን ያፀደቀው ደንብ ቤት ወራሾች ወይም ቤት ገዢዎች ስም ዝውውር ሲጠይቁ ለፈንዱ የሚውል ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፤
የመሬት ይዞታ መብት በሙሉ ወይም በከፊል በሽያጭ፣ በስጦታ፣ በዓይነት መዋጮ ወይም በሌላ ህጋዊ መንገድ በመተላለፉ፣እንዲሁም የመሬት ይዞታ መብት በውርስ በመተላለፉ ምክንያት የስም ዝውውር ሲፈጸም በእያንዳንዱ ግብይት ወይም አገልግሎት ላይ ለፈንዱ እንዲውል የሚከፈል ተጨማሪ ክፍያ ነው፤
በዚህም መሠረት ዜጎች የከተማ መሬት ይዞታ መብት በማናቸውም ሕጋዊ መንገድ ለሌላ ሰው በመተላለፉ የስም ዝውውር ሲፈፀም ከግብይቱ ዋጋ ዜሮ ነጥብ ሦስት ከመቶ /ዐ.3%/፤እንዲሁም የመሬት ይዞታ መብት በውርስ የስም ዝውውር ሲፈፀም በውርስ በተላለፈው ይዞታ ላይ ካለው የማይንቀሣቀስ ንብረት ዋጋ ግምት ዜሮ ነጥብ አንድ ከመቶ /ዐ.1%/፣ /ወራሽ ከአንድ በላይ ከሆኑና ውርሱን ከተከፋፈሉ በሚደርሣቸው የውርስ ድርሻ አግባብ ተፈፃሚ እንደሚሆን ደንቡ ይገልፃል፡፡
ክፍያው ለእያንዳንዱ የአገልግሎት ዓይነት የሚፈፀም ክፍያ ሲሆን ለእያንዳንዱ አገልግሎት ለየብቻ የስም ዝውውሩ ከመፈፀሙ በፊት መከፈል እንዳለበት ቁም ነገር ሚዲያ የተመለከተው ደንብ ያስገድዳል፡፡
በዚህ መሠረት 10 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ቤት የገዛ ሰው ከስም ዝውውሩ በፊት 30 ሺ ብር ለፈንዱ መክፈል ያለበት ሲሆን 20 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ቤት የሚወርስ ሰው ደግሞ 20 ሺ ብር እንዲሁም ወራሾች ከአንድ በላይ ከሆኑ እያንዳንዳቸው 20 ሺ ብር በስማቸው ካልከፈሉ የስም ዝውውር እንደማይፈፀምላቸው ተመልክቷል፡፡

