በቅርቡ በቬንዙዌላ የመንግስት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ፣ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ከተፈራረመችው የ50 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ሽያጭ ስምምነት የመጀመሪያውን 300 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን በይፋ አስታውቀዋል።
ይህ ገቢ የተገኘው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ቬንዙዌላ 50 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለአሜሪካ እንድታቀርብ ካደረጉት ስምምነት ነው። ትረምፕ እንደተናገሩት፣ አሜሪካ ነዳጁን ተረክባ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እየሸጠችው ሲሆን፣ ከሽያጩ የሚገኘው ገቢም ለቬንዙዌላ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ እየዋለ ነው።
300 ሚሊዮን ዶላሩ በኳታር በሚገኝ ባንክ በኩል በአገሪቱ ለሚገኙ አራት የግል ባንኮች እና ለብሔራዊ ባንክ የሚከፋፈል ይሆናል። ገንዘቡ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን ለመቅረፍ፣ የሸቀጦች ዋጋን ለማረጋጋት እና የሰራተኞችን የመግዛት አቅም ለመጠበቅ እንደሚውል ዴልሲ ሮድሪጌዝ ገልጸዋል።
የብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ሮድሪጌዝ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የነዳጅ ሕግ ላይ ትልቅ ማሻሻያ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ይህ አዲስ ሕግ የውጭ ኩባንያዎች (እንደChevron እና ExxonMobil ያሉ) በቬንዙዌላ የነዳጅ ቁፋሮ ላይ ሰፊ ድርሻ እና ቁጥጥር እንዲኖራቸው የሚፈቅድ “የአጋርነት ሞዴል” (Partnership Model) ላይ የተመሰረተ ነው።
ይህ የኢኮኖሚ ዕንቅስቃሴ የመጣው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ ልዩ ሃይል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ዴልሲ ሮድሪጌዝ በጊዜያዊነት ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ነው።
ፕሬዝዳንት ትረምፕ “የቬንዙዌላን የነዳጅ ኢንዱስትሪ እኛ ነን የገነባነው፣ አሁን ደግሞ መልሰን እየተረከብነው ነው” በማለት የአገሪቱን የነዳጅ ዘርፍ በቀጥታ የመቆጣጠር ፍላጎት አሳይተዋል። ይህ 300 ሚሊዮን ዶላር ለቬንዙዌላ ኢኮኖሚ ትልቅ ትንፋሽ ቢሆንም፣ አገሪቱ በሃብቷ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት እና የአሜሪካን ተጽዕኖ በተመለከተ ከፍተኛ ክርክር እያስነሳ ይገኛል።
ቬንዙዌላ ከአሜሪካ ጋር በገባችው የነዳጅ ስምምነት የመጀመሪያውን 300 ሚሊዮን ዶላር አገኘች

