የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማራዘማቸውን አስታወቁ። ፕሬዝዳንቱ “ኦፕሬሽን ሚድናይት ሀመር የኢራንን የኒውክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ማውደሙን ገልጸው፣ የኒውክሌር ቁሳቁሶችን የማጽዳቱ ሥራ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ጠቁመዋል። አክለውም አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር በመጨረሻ “በጣም ጥሩ ስምምነት” ያስገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፣ የቴል አቪቭ መንግሥት አሜሪካ እና ኢራን ወደ ስምምነት ሊደርሱ አይችሉም የሚል እምነት አለው።
የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ለኢራን ንግግር ወደ ኢስላማባድ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ “ታግዷል”። ፓኪስታን በበኩሏ የኢራን ልዑክ በኢስላማባዱ ድርድር ላይ ስለመሳተፉ ይፋዊ ምላሽ እየጠበቀች ሲሆን፣ እርግጠኛ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥም ሆና ለሁለተኛው ዙር የአሜሪካ-ኢራን ንግግር ዝግጅት እያደረገች መሆኑን አስታውቃለች።
የኢራኑ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሳቪ፣ የባህረ ሰላጤው አገራት ግዛታቸውንና የአየር ክልላቸውን በኢራን ላይ ለሚሰነዘር ጥቃት እንዳይፈቅዱ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። በተጨማሪም በባህረ ሰላጤው አካባቢ ከሚገኙ የኃይል (ኢነርጂ) ተቋማት መካከል 34ቱ በከፍተኛ ሁኔታ መውደማቸው ታውቋል።//
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱ የተራዘመው በፓኪስታን መሪዎች ጥያቄ መሆኑን ተናገሩ።
የኢራን ተወካዮች ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል “የተዋሃደ የሰላም ሃሳብ” እስኪያቀርቡ ድረስ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገውን የተኩስ አቁም ለድርድር ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት ማራዘማቸውን ቢናገሩም፣ በሀገሪቱ የወደብ ላይ የተጣለው የአሜሪካ ባህር ኃይል እገዳ ግን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢራን ግጭቱን ለማስቆም የሚያስችል የሰላም ሃሳብ ይዛ እስክትመጣ ድረስ “የተኩስ አቁሙን እንደሚያራዝሙ” ገልጸው፤ ሆኖም “ወታደራዊ ኃይላችን እገዳውን እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ብለዋል። የትራምፕ የተኩስ አቁም ማራዘሚያ ውሳኔ የተሰማው ስምምነቱ ያበቃል ተብሎ ከታሰበ ጥቂት ሰዓታት በፊት ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኋይት ሀውስ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ለሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር ወደ ፓኪስታን እንደማይጓዙ አስታውቋል። ፕሬዝዳንቱ የንግግሩ መቋረጥ በኢራን የውስጥ አለመግባባት ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፣ የፓኪስታን መሪዎች ግን የተኩስ አቁሙ እንዲራዘም እንደጠየቋቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ በTruth Social ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “የኢራን መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ የተከፋፈለ መሆኑን መነሻ በማድረግ — ይህም ያልተጠበቀ አይደለም — እንዲሁም በፓኪስታን የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እና በጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ ጥያቄ መሠረት፣ የኢራን መሪዎች እና ተወካዮች የተዋሃደ የሰላም ሃሳብ እስኪያቀርቡ ድረስ በሀገሪቱ ላይ የምናደርገውን ጥቃት እንድንቆይ ተጠይቀናል።”
ይሁን እንጂ በሆርሙዝ ስትሬት አቅራቢያ ባሉ የኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ እንደማይነሳና የአሜሪካ ጦር “በሌሎች በኩል ዝግጁ ሆኖ እንደሚቆይ” ትራምፕ አስታውቀዋል። የተኩስ አቁሙ የሚቀጥለው “የእነርሱ ሃሳብ ቀርቦ ውይይቶች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እስኪጠናቀቁ ድረስ ነው” ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢራን ባለስልጣናት አሜሪካ በተኩስ አቁሙ መጀመሪያ ላይ በወጣው ባለ አስር ነጥብ ማዕቀፍ ላይ የገባችውን ቃል ጥሳለች ሲሉ ይከሳሉ።
ለዓለም አቀፍ የነዳጅ ፍሰት ወሳኝ በሆነው በሆርሙዝ ስትሬት ላይ ያለው አለመግባባት ዋነኛው የጭቅጭቅ መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል። ኢራን በግጭቱ መጀመሪያ ላይ ይህንን መስመር ዘግታው የነበረ ሲሆን፣ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የተቀበሉት የባህር መስመሩ ሙሉ በሙሉ እንዲከፈት በሚል ቅድመ ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል።
ሆኖም አሁንም ድረስ በመስመሩ ላይ ያለው የመርከቦች እንቅስቃሴ እጅግ አነስተኛ ነው። የመጀመሪያው ዙር ንግግር ከከሸፈ በኋላ የአሜሪካ ባህር ኃይል በውሃ መስመሩ አቅራቢያ በሚገኙ የኢራን ወደቦች ላይ ከበባ ማድረጉ ይታወሳል።//
ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማራዘማቸውን አስታወቁ

