ትንሿ ባለ ማዕረግ -ረዳት ኮሚሽነር ጥሩነሽ ዲባባ !

ነገር የገባት ሰጎን፥ የኦሊምፒክ የሶስት ወርቅና ሶስት ነሀስ ባለቤት፥ የአለም ሻምፒዮና የአምስት ወርቅና አንድ ብር አሸናፊ፥ የወድቆ መነሳት ተምሳሌት፥ ከህመም ታግሎ ሃገርን የማኩራት ማሳያ፥ ኢትዮጵያዊቷ ጀግኒት አዲስ የማዕረግ እድገት አግኝታለች
ረዳት ኮሚሽነር ጥሩነሽ ዲባባ ቀነኒ!
የስፖርት፣ የሙዚቃና የቲያትር ቡድኑን 40ኛ አመት እያከበረ የሚገኘው የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የ41 አመቷን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ከኮማንደርነት ወደ ረዳት ኮሚሽነርነት አሳድጓታል፤ በዚህም በተቋሙ የስፖርት ክለብ ታሪክ ለዚህ ክብር የበቃች በእድሜ ትንሿ ረዳት ኮሚሽነር ለመሆን በቅታለች
ረዳት ኮሚሽነር ከኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር ቀጥሎ ሶስተኛው ማዕረግ ሲሆን ጥሩነሽም በፌደራል ማረሚያ ስፖርት ክለብ ሶስተኛዋ ረዳት ኮሚሽነር ሆናለች፤ ከዚህ ቀደም በሴቶች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት የኦሊምፒክ ባለወርቋ ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም 7 ኦሊምፒክና 12 የአለም ሻምፒዮና ላይ በአሰልጣኝነት ያገለገለው ሁሴን ሽቦ የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግን ማግኘታቸው ይታወሳል
በዝግጅቱ የጥሩነሽ ባለቤት፥ የሁለት የኦሊምፒክና የሶስት የአለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊስቱ የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስለሺ ስህን በፌደራል ማረሚያ ቤቶችና በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነውን ኒሻን ተሸልሟል፤ ስለሺ የኮማንደር ማዕረግም አለው፤ አሰልጣኝ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦም በተመሳሳይ ከፍተኛውን ኒሻን ተሸልሟል
በተጨማሪ ኮማንደር ፋጡማ ሮባ፣ ኮማንደር ሰለሞን ባረጋና ምክትል ኮማንደር ሰንበሬ ተፈሪ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል
በሀገራችን በስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ በመያዝ ጥሩነሽና ቤተሰቦቿ ቀዳሚ ሆነዋል፤ ጥሩነሽ ዲባባና አክስቷ ደራርቱ ቱሉ ረዳት ኮሚሽነሮች ናቸው፤ ባለቤቷ ስለሺ ስህን ደግሞ ኮማንደርና የከፍተኛ ኒሻን ተሸላሚ ነው፤ በሩጫው አለም ደማቅ ታሪክ የፃፈው ይህ ቤተሰብ አሁን ደግሞ በክብር ማዕረግ ማሸብረቁን ቀጥሎበታል፥ እንኳን ደስ አላችሁ!
(ታምሩ ዓለሙ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe