ቻይና የዶላርን የበላይነት ለመቀዳጀት እንዳሰበች ተሰምቷል፡፡ በዚህ ወቅት አዲስ የገንዘብ ፉክክር በዓለም መድረክ ላይ እየታየ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ሺ ቻይና ገንዘቧን በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫዎት እንዲችል ማድረግ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ የቻይናው ገንዘብ ዩዋን እንዲጠናከርና የአሜሪካ ዶላር ያለውን ዓለም አቀፍ የበላይነት እንዲገዳደር ያላቸውን ግልጽ ፍላጎት በይፋ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ስዓት አብዛኛው ዓለም አቀፍ ንግድ የሚከናወነው በዩኤስ ዶላር መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአሜሪካ ዶላር አሁን 58 በመቶ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ የገንዘብ መጠባበቂያ ክምችት በመያዝ ቀዳሚ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የቻይናው ገንዘብ የዓለም መጠባበቂያ ክምችት ውስጥ የ2 በመቶ ነው ድርሻ ይዞ የሚገኘው፡፡ በርግጥ በዚህ ወቅት የበርከታ ሀገራት ማዕከላዊ ባንኮች ፊታቸውን ዶላር ከመግዛት ይልቅ ወደ ወርቅ እያዞሩ ነው፡፡ ሀገራቱ ይህን የሚያደርጉት ከማዕቀብ እና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችልን አደጋ ለመቀነስ በሚል ነው፡፡
ወርቅን አንዲት ሀገር ብቻ በባለቤትነት ይዛው የምትገኝ ማዕድን ባለመሆኑ ሀገራት ከስጋት ነጻ ለመሆን በሚል ፊታቸውን እንዲያዞሩ እያደረጋቸው ነው ተብሏል፡፡
ቻይና አሁን ይህንን ነው መለወጥ እፈልጋለሁ ያለችው፡፡ ይህንን ግብም ለማሳካት ፕሬዝዳንት ሺ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሳካት አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጠንካራ የሆነ ማዕከላዊ ባንክ መገንባት፡ጠንካራ የሆነ የፋይናስ ስርዓት መዘርጋት፡ተወዳዳሪ የሆኑ ባንኮችን መፍጠርና ግሎባል የሆኑ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የእስቶክ ማርኪቱን ማብቃት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን እቅዳቸውን ለባለስልጣናቶቻቸው ያሳወቁት በ2024 ቢሆንም ለመላው ህዝብ ግን ይፋ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ አሁን ይህን ማሳወቅ የፈለጉት ያለምክንያት አይደለምም ተብሏል፡፡ ምን አልባትም በዚህ ስዓት የዩኤስ ዶላር በጫና ውስጥ ስላለ የሚል ግምት ይዘው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ባለፈው አንድ ወር ገደማ ዶላር የመዳከም ሁኔታ እየገጠመው በመሆኑ ፕሬዝዳንቱ ለዓለም ምርጫ እንዳለ ለማሳየት ጊዜውን መርጠውታል የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡
ይህም ሆኖ ግን የዩኤስ ዶላር ከ6 ትሪሊየን በላይ በማዕከላዊ ባንክ በመጠባበቂያነት ይገኛል፡፡ ከአሜሪካ ዶላር ቀጥሎ በበቂ ሁኔታ ክምችት የሚገኘው ዩሮ ሲሆን በሦስተኛነት ደግሞ የጃፓን የን ነው፡፡//

