የቻይና የሮኬት ሳይንቲቶች ከባድ የሆኑ ሮኬቶችን በመጠቀም በጠፈር ውስጥ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‘የማይታመን ፕሮጀክት’ የተባለለት ፕሮጀክት ወደ ተግባር ከተለወጠ በምንም ሁኔታ የማያቋርጥ ኃይል ከፀሐይ ለማግኘት እንደሚያስችል ነው የተጠቀሰው። አንድ ከፍተኛ የቻይና ሳይንቲስት በጠፈር ውስጥ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ለመገንባት የታቀደውን ፕሮጀክት “ከምድር በላይ ያሉ ሦስት የሸለቆ ግድቦች ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። በጠፈር ላይ የሚሠሩት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከፀሐይ ኃይል ሰብስበው ወደ ምድር በማስተላለፍ የማያቋርጥ ኃይል ያቀርባሉ ተብሏል። በዚህም የኃይል ማመንጫው የቀን እና ሌሊት ዑደትን ጨምሮ ወቅቶች ሳይገድቡት የማያቋርጥ ኃይል ከፀሐይ መሰብሰብ እንደሚችል ነው የተገለጸው። ለሀሳቡ መነሻ የሆነው በሕዋ ውስጥ ያለው የኃይል ጥልቀት በምድር ገጽ ላይ ካለው በአማካይ 10 እጥፍ እንደሚበልጥ በጥናት በመረጋገጡ መሆኑን ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል። ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኃይል ዘርፉ “የማንሃተን ፕሮጀክት” ተብሎ እንደሚጠራ ነው የተጠቀሰው።

