ኢራን የአሜሪካን ጥቃት በማስመልከት ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጠች፡፡
በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ያለው ውጥረት አዲስ ማዕራፍ ላይ የደረሰ መስሏል፡፡ የኢራን ባለስልጣናት በመሠረተ ልማቶቻቸው ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም ጥቃት የማያዳግም ዋጋ እንደሚያስከፍል በይፋ አስታውቀዋል፡፡
በኢነርጂ እና በሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ ምላሹ ሁሉን አቀፍ እና ካባድ እንደሚሆን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል፡፡
ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ነገ ማክሰኞ በቀነ ገደብነት ካስቀመጡ በኋላ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በአገራቸው ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ከደረሰ ምላሻቸው ከባድ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
አባስ አራግቺ አሜሪካ ያለጥርጥር ከኢራን ጦር ሃይሎች የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ ምላሽ ይጠብቃታል በማለት ለፈረንሳዩ አቻቸው ገልጸውላቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ የደህንነት አዛዥ መገደላቸው ተሰማ፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የደህንነት አዛዥ የሆኑት ማጂድ ካዴሚ ዛሬ ጠዋት መገደላቸውን የሀገሪቱ መንግስታዊ የመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢራን ለግድያው እስራኤልን እና አሜሪካን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን እስራኤልም በበኩሏ ለጥቃቱ ሀላፊነቱን ወስዳለች፡፡
አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ ማጂድ የተገደሉት በእስራኤል እና በአሜሪካ በተቀነባበረ ጥቃት መሆኑን ገልጻል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሃይል በቴሌግራም ባወጣው መግለጫ ግድያው ለኢራን አብዮታዊ ዘብ ሌላ ከባድ ኪሳራ መሆኑን በመጥቀስ ነው ሃላፊነቱን የሰወደው፡፡
ኢራን አብዛኛውን ጊዜ የከፍተኛ ባለስልጣኖቿን ግድያ የምታረጋግጠው እስራኤልና አሜሪካ መረጃውን ካወጡ በኋላ ቢሆንም፤የካዴሚን ግድያ ግን በራሷ ተነሳሽነት ቀድማ ይፋ አድርጋዋለች፡፡
ማጂድ ካዴሚ ባለፈው ጥር ወር በኢራን የተቀሰቀሰውን መጠነ ሰፊ ተቃውሞ አሜሪካ እና እስራኤል እንዳቀጣጠሉት ሲከሱ የነበሩ ሰው መሆናቸውም ይታወሳል፡፡//

