አርቲስት ተሾመ አሰግድ “የኔን የህይወት መስመር እግዚአብሔር በመልካም ሲያበጅልኝ ነው የኖረው”

ተሾመ አሰግድ በ1942 ዓ.ም ነው በድሮዋ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የተወለደው። አሁን 75ኛ ዓመቱን ይዟል። ገና የአምስት ወር ልጅ እያለ የአይኑን ብርሃን ያጣው ተሾመ እናት ሆነው ያሳደጉት በዝምድና ቋጠሮ አክስት በወል ግን እናቱ የሆኑት ወይዘሮ አማካለች ይመር ናቸው። ስድስት ወንድ እና ስምንት ሴት በተወለደበት ቤተሰብ ውስጥ ተሾመ ለአቶ አሰግድ ይመር አራተኛው ልጅ ነው። ምንም እንኳን በአክስቱ ወ/ሮ አማከለች ጥረት፣ የመንደሩን ልጆች የኔም ናቸው ብሎ በሚያሳድገው ጎረቤት ክብካቤ ቢያድግም ተሾመ ራስን መቻል ይሉትን ጥበብ፣ በገዛ እግር መቆም ይሉትን ብልሃት ገና ብላቴና ሳለ ነው የሚያውቀው። በደምቢዶሎ ቡና በረንዳ ከትላልቆቹ ነጋዴዎች ጆንያ ሾልኮ የሚፈስ ቡና እየለቀመ በመሸጥ ትምህርት ቤት ሲሄድ የሚያጌጥበትን ሸራ ጫማ መግዛት ችሎ ነበር። ተሰጥኦ የሚሉት መክሊት ገና በጠዋቱ እድል ፈንታውን ያሰመረለት ተሾመ በመንደሩ ሰርግ ቤቶች አይታጣም ነበር።

“የኔን የህይወት መስመር እግዚአብሔር በመልካም ሲያበጅልኝ ነው የኖረው” ብሎ የሚያምነው ተሾመ አሰግድ፤ ሚስተር ራሰል ከሚባሉ ኦሮሚኛን አቀላጥፈው ከሚናገሩ ካናዳዊ የወንጌል መምህር ጋር የተገናኘባትን ጀምበር የዛሬ ማንነቴ መሰረት የተጣለባት ነች ይላል። እኚህ ሰው ተሾመን ገና በስድስት ዓመቱ መንገድ አግኝተውት ይህ ህፃን ትምህርት ማግኘት አለበት ብለው ጂፕ መኪናቸው ውስጥ አስገብተው ይዘውት ተፈተለኩ። አዲስ ነገርን የመከተል የልጅነት ጉጉት የኋሊት ወደቤተሰቦቹ ጎትቶ ያላስቀረው ተሾመም ሚስተር ራሰልን በፈቃደኝነት ተከተላቸው። #በሃገሩ ወግ ባህል ወደ ሰውነቱ ይዘልቅ የጀመረው የጥበብ እርሾ ከፈረንጁ ዘመናዊ የሙዚቃ ዕውቀት ጋር ተዋህዶ የወደፊት የሙያ እንጀራው ይጋገር ዘንድ ተሾመ ገና በልጅነቱ ከታች በእግር እየተረገጠ ከሚሰራው የድሮ ፒያኖ ጋር ተዋወቀ። ይህ የሆነው የሚስተር ራሰል ባለቤት ቤቷ ይህንን የሙዚቃ መሳሪያ ትጫወት ስለነበር ነው። ፒያኖውን ስትጫወት እስሩዋ ሆኖ በአርምሞ ያዳምጣት የነበረው ይህ ልጅ እሱዋ ዘወር ስትል ተደብቆ የልጅ ጣቶቹን ፒያኖው ቁልፎች ላይ ያሩዋሩጣቸው ጀመር። ገና በአስራ ሶስት ዓመቱ ጥሩ ሙዚቃ መጫወት የመቻሉ ሚስጥር ቋጠሮ እንዲህ ባሉ የትላንት ወዲያ ታሪኮቹ ውስጥ ነው የሚገኙት። #ቁምጣ፣ ጥብቆና ሸሚዝ ተገዝቶለት በትምህርት ቤት ገበታ ሊቀመጥ የቻለው ተሾመ ማየት ለሚችሉት ብዙ ቦታዎችን ለአይነ ስውራን ደግሞ ጥቂት ቦታዎችን አሰናድቶ ያስተምር በነበረው የአሜሪካን ሚሽን ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። እናም እስከ አስር ዓመት እድሜው ድረስ እዚያው ተማረ። አንድ ቀን በአጋጣሚ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ተሾመ የሚማርበትን ትምህርት ቤት ለመጎብኘት ደምቢዶሎ ይሄዳሉ። ህፃናቱን እየዞሩ እያናገሩ ነበርና ለታዳጊው ተሾመም ጥያቄዎችን አቀረቡለት። በኦሮምኛ ነበር ያናገሩት። “ኦሮምኛ ትችላለህ?” የሚለውን ጥያቄ አስቀድመው “እኛ ማን ነን?” ብለው ጠየቁት። እሱም ምን ልጅ ቢሆን ወቅቱ የሚፈልገውን ቋንቋ ያውቅ ነበርና “የኢትዮጵያ ብርሃን ግርማዊ ጃንሆይ” አላቸው። “ምን እንድናደረግልህ ትፈልጋለህ?” ጠየቁት። በወቅቱ ከፍተኛ የመሰለውን ነገር እንዲፈፅሙለት ነገራቸው። ንጉስ ነበሩና አልከበዳቸውም። #ሸራ ጫማው ተገዛለት።የሚማርበት ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን ይዞ ይጓዝበት የገንዘብ አቅም ስላለነበረው ጥያቄውን ለቀዳማዊ ሃይለስላሴ አቅርቦ ከስምንት ተማሪዎች ገሚሶቹ ወደ ባኮ ሲሄዱ ገሚሶቹ ደግሞ ወደ ሰበታ ተሸኙ። ተሾመ ለሶስት ዓመታት ባኮ ቢቀመጥም ለጆሮ ህክምና ስዊድን ደርሶ ከመጣ በሁዋላ ወደ ሰበታ ተዛወረ። #በወቅቱ አጠራር “መርሃ ዕውራን” ተብሎ በሚታወቀው ትምህርት ቤት ዛሬ በካናዳ ከሚኖረው አብዱቄ ከፈኔ እና ከሌሎች ባልንጀሮቹ ጋር ሙዚቃን በቅጡ መለማመድ ጀመረ። የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርን ጨምሮ እነ ፕሮፍሰር አሸናፊ ከበደ፣ ተስፋዬ ለማ፣ ዓለማየሁ ፋንታ እና መላኩ ገላውን የመሰሉ ሰዎች ተሾመን በማበረታቱ እና የሙያ ፈር በማስያዙ ረገድ በኩል ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።እናም ገና በወጣትነቱ ፍሬውን ማየት ማሳየት ጀመረ። ከስድስት የሰበታ አይነ ስውራን ትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ “ሬንቦው” የተባለ ቡድን አቋቁመው ለረዥም ጊዜ ሰርተዋል። “ይህች አጋጣሚ” የተሰኘው የጥላሁን ገሰሰ ዜማ አስቀድሞ ተሾመ አሰግድ ገና በለግላጋነቱ ሊጫወተው የነበረ ዜማ ነው። #በአሁኑ ሰዓት ዊስኮነሰን የሚኖረው የህግ ባለሙያ ዶክተር በቀለ ሃይለየሱስ የደረሰው ይህ ስራ በመጀመሪያ ሊቀነቀን የነበረው በተሾመ አሰግድ ቢሆንም የፊሊፕስ ኩባንያ ባለቤት በተፅዕኖ ዜማው ለጥላሁን ገሰሰ እንዲሰጥ ቢያደርጉም ጥላሁን የተሾመን ያማረ አጨዋወት አይቶ የገበያው መሪ ባለሃብት የወሰኑትን መቀልበሱ ባይቻለው እንባውን አፍስሶ ከሙዚቃ ሽያጩ ያገኘውን ሙሉ ገቢ በወቅቱ እሱን ላጀቡት ለእነ ተሾመ አሰግድ – ለሬንቦ ባንድ ሰጥቷል። #ተሾመ “ውጋጋን” በተባለው የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር የሙዚቃ ቡድን ውስጥም አገልግሏል። ተሾመ ከውጭ የትምህርት ቆይታው በኋላ ሙያዊ አበርክቶውን ከለገሰባቸው ተቋማት መካከል የዓይነ ስውራን ማህበር አንዱ ሲሆን አመራር በመስጠትም ሙያዊና ወገናዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል። #ተሾመ እንደአብዛኛው የወቅቱ ወጣት በእድገት በህብረት ዘመቻ ተሰልፎ ነበር። ያንን የወቅቱን ግዴታ ከተወጣም በኋላ ነበር ጀርመን አገር ሄዶ የፒያኖ ቅኝት እና ፒያኖ አሰራር ትምህርቱን የተከታተለው። አሁን ኬምኔትስ ተብላ በምትጠራው፤ በቀዝቃዛው ጦርነት የበርሊን ግንብ ዘመን ካርል ማረክሽታት ትባል በነበረችው ከተማ በብሎንደን ሴነትሩም ወይም የዓይነ ስውራን ትምህርት ማዕከል ነበር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1980 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ምዕራፍ የተቀላቀለው። የጀርመንኛ ቋንቋን ያጠናበትን ስድስት ወር ጨምሮ በአጠቃላይ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ነበር ተሾመ ትምህርቱን በጀርመን ሃገር ተከታትሎ በዲፕሎም የተመረቀው። #ተሾመ ትምህርቱን በብቃት ጨርሶ ሃገሩን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ በመንፈሰ ሙሉነት ተመልሶ በቅድሚያ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ነበር ያቀናው። ተቋሙ ግን በልምድ ከሌላ መምህር የተማሩትንና በዘልማድ የሚሰሩትን ዓይናማ ሰው በፒያኖ ቃኚነት ቀጥሮ እያሰራ በጀርመን ሃገር ትምህርት ቤት ገብቶ ሙያውን በብቃት ቀስሞ የመጣውን ተሾመ አሰግድን አልፈልግህም አለው። ለነገሩ ይህ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንደ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አይነት በእኩልነት የሚያምኑ ሰዎች የነበሩበት መሆኑ ባይታበልም አይነ ስውራን ሙዚቃን መማርም ሆነ ማስተማር አይችሉም በሚል እና እነሱን ተቀብለን ለማስተናገድ በበቂ አልተዘጋጀንም በሚል አስባብ እስከዘንድሮ አይነ ስውራንን ከሙዚቃ ትምህርት ገበታ ነጥሎ ኖሯል። #ተሾመ ግን በዚያ መገፋት ተስፋ ሳይቆርጥ የባህል ሚኒሰቴርን እና ቴአትር ቤቶችን በር ደጋግሞ አንኳኳ።የእነዚህ ተቋማት በሮች በዋናነት ለዓይናማዎቹ ብቻ የተከፈቱ ነበሩና ማንኳኳቱ ተሰምቶ በሮቹ አልተከፈቱለትም። ተሾመ ግን “አንኳኩቻለሁ፤ በሮቹ ግን አልተከፈቱም” ብሎ መቆዘምን፣ ቀያጅ የሆነው የማህረሰቡ አስተሳሰብ የሚፅፍለትን ዕጣ መቀበልን ምርጫው አላደረገም። የማይከፈቱ በሮችን ከማንኳኳት ይልቅ ሌሎች በሮችን ወደ መስራት ሄደ። በተለያዩ ባንዶች ውስጥ ማገልገሉን፣ ከእውቅ ሙዚቀኞች ጋር ተባብሮ መስራቱን ቀጠለ። በኋላም ጎረቤት ሃገር ጅቡቲን መኖሪያው አደረገ። ለነገሩ ወደዚያም ሄዶ መስራት ዋዛ አልነበረም። ከሃገር እንዳይወጣ በሮችን ሊቆልፉበት የታገሉም ነበሩ። ማመልከቻው በአንድ ባለስልጣን ጠረጴዛ ላይ ልታርፍ በመቻሉዋ ነበር የጅቡቲ ጉዞውም በመጨረሻ የተሳካው። #በጅቡቲ የአምስት ዓመት ቆይታው “የኩባያ ወተት” የተሰኘ ስራው ገንኖ ቢወጣም ተሾመ የተለያየ ሃገር ዜጎችን ለማዝናናት በተለያዩ ቋንቋዎች ያዜም ነበር። እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማልኛ እና ሌሎችም።ተሾመ በሙዚቃ ቅንብር በኩል ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ጋር ስራዎችን አበርክቷል። ከነዚህም ውስጥ ለጥላሁን ገሰሰ ያቀናበራቸው “አልማዝን አይቼ”፣ “ያለቀሰ ሲስቅ” እና “ውቢት ህይወቴ ነሽ” የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው። በተጨማሪም በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ቆይታው የፀሐይ እንዳለን ዜማም አቀናብሯል። ይህም ሆኖ ግን ተሾመ ቅንብርን በሙሉ መንፈስ ስራዬ ብሎ የያዘው በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የራሱን የድምፅ አሻራ ካተመው ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር ሲሰራ እንድሆነ ይናገራል። #ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ታደሰ ከህዝብ ጋር በሰፊው ያስተዋወቀው ስራው የሉባንጃዬ ካሴቱ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚያ ካሴት ውስጥ በዜማም ሆነ በግጥም እንዲሁም በቅንብር የሚገደፍ አንድም ስራ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም። እንደ ሉባንጃዬ እና ቀን ሳይመሽ ሳይጨልም በጊዜን የመሳሰሉት ምርጥ ስራዎች የተካተቱበትን ይህንን ሙሉ ስራ ያቀናበረው ተሾመ አሰግድ ነው።በኋላም የሂሩት በቀለን ልጅ የመስፍን ኤልያስን እና ጥላሁንን ይተካል በሚል ማሞካሻ ይሞገስ የነበረውን ነገር ግን በልጅነቱ በሞት የተቀጨውን የደሳለኝ ቢሻውን ካሴቶችም አቀናብሯል። #ኪቦርድ ወይም ሲንተሳይዘር የሚባለውን መሳሪያ በመጫወትም ድምፃውያንን አጅቧል።የሙዚቃ መሳሪያዎች ጨዋታ ከተነሳ የተሾመ ችሎታ ሊወሳ ግድ ነው። ተሾመ ክራር፣ መሰንቆ፣ ዋሽንት፣ አኮርዲዮን፣ ፒያኖ- ኪቦርድ የመሳሰሉትን መሳሪያዎች ይጫወታል። #አርቲስት ተሾመ አሰግድ በግልና በጋራ በአጠቃላይ ስድስት አልበሞችን ለህዝብ አበርክቷል።

  1. “ትዝታ”፡ ከሬንቦው ባንድ ጋር በመሪ ድምፃዊነት ፊሊፕስ ባስቀረፀው ሸክላ
  2. “በላሽው”፡ የካሴት ስራ ከሬንቦው ባንድ ጋር
  3. “የኩባያ ወተት”፡ ከሮሃ ባንድ ጋር
  4. “ደርባባዬ”፡ ከሮሃ ባንድ ጋር
  5. በቡድን ከኬኔዲ መንገሻ እና ራሄል ዮሐንስ ጋር
  6. በቡድን ከነበዛወርቅ አስፋው፣ ኤሊያስ ተባባልና ማርታ አሻጋሪ ጋር #ተሾመ በተናጥል ተወዳጅ ከሆኑለት እና ዛሬ ድረስ ወጣቶችን እያነቃቁ ከሚገኙት ዜማዎች መካከል “የኔ አካል የኔው ነሽ”፣ “አገሬ ነገር የዛው ሙዳይ”፣ “እንዲያው ዘራፌዋ”፣ “ያዘልቃል ያልሽው ፈጣን መኪና” እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው። #ተሾመ አሰግድ በግሪክ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ሆላንድ፣ ስዊድን፣ ጅቡቲ፣ ካናዳ እና እንግሊዝ ሃገራት የሚኖሩ አድናቂዎቹን በሙዚቃ ስራዎቹ የደረሰ ሲሆን፤ በሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ማለት በሚባል ደረጃ ተፈጥሮ በለገሰችውና በዘመናት ልምድና ችሎታው ሲያገለግለን ኖሩዋል። @አዲስ1879

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe