ክብር ሽልማት ደራስያንና የሚዲያ ባለሙያዎችን የሚሸልም ዓመታዊ ዝግጅት ሲሆን ግንቦት ዘጠኝ 2016 በግሮቭ ጋርደን በተደረገው የክብር ሽልማት መርሐ ግብር ላይ አቶ አማረ አረጋዊ በጋዜጠኝነት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኗል።
ክብር ሽልማት 16 ዘርፎችን የያዘ ሲሆን ዘጠኙ የደራስያን ሰባቱ የሚዲያ ባለሙያዎችን በማወዳደር የሚሸልም ሲሆን አቶ አማረ አረጋዊም የክብር ሽልማት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል።
የሪፖርተር ጋዜጣ መስራች አቶ አማረ በ1962 የዊንጌት ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ እንግሊዝ ሀገር የነጻ የትምህርት እድል አግኝቶ ይሄዳል፡፡ እዚያም ለተወሰኑ አመታት ትምህርቱን ሲከታተል ቆየ፡፡ ከ1973-1983 በትግል ውስጥ ያሳለፈ ሲሆን ከ1983-1985 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ሀላፊ እንዲሁም ከ1985-1987 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ መሪ በመሆን አገልግሏል፡፡
በ1987 ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደለቀቀ ሪፖርተር ጋዜጣን በመመስረት እስከዛሬ ድረስ ወጣትና አንጋፋ ባለሙያዎችን በማፍራት ይገኛል፡፡ ሽልማቱን የቁም ነገር መጽሄት ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ሃይሉ ተቀብሎለታል፡፡
አርብ ግንቦት 9 2016 ዓ.ም በግሮቭ ጋርደን ዎክ በተደረገው ታላቅ ሥነ- ስርአት 16 የሚድያ እና የድርሰት ሰዎች የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በክብር እንግድነት በተገኙበት በተደረገው የሽልማት መርሀ ግብር ታላላቅ እንግዶችም ታድመዋል።
የሽልማቱ ሀሣብ አመንጪ እና የቃል መልቲ ሚድያ ባለቤት ደራሲ ቃል ኪዳን ሀይሉ ባደረገው ንግግር የሠራን የማመስገን ባህል ሊለመድ ይገባል ብሏል። የሽልማት ሂደቱም ሙያዊነትን እና ጥናትን መሠረት አድርጎ መካሄዱን ተናግሯል ።
ክብር ሽልማት በሥነጽሑፍ የሕይወት ዘመን ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕልን፤ በምርጥ ልብወለድ ደራሲ ገላጋይን፤ የአመቱንምርጥ የሚዲያ ባለሙያን ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ፤ ምርጥ የመዝናኛ ዝግጅት አቅራቢ እስካለ ተስፋዬን እና ሌሎች ዘርፎችን በመሸለም ተጠናቅቋል።

