አይኔን ተመልከተኝ

አይኔን ተመልከተኝ (በዶ/ር ዮናስ ባህረጥበብ)

ልጄ የልጅ እዳ

ልጄ የልጅ ፍቅር

ገላህን አጥቤ ቁርስህን አብልቼ

አሰርኩህ በጋቢ…

እንዳትጎዳብኝ

እኔ የምችለው ላንተ የሚገባ የሚያስፈልግ ነገር

ስመጣ እንዳገኝህ ካልጋ እንድትቆየኝ በጋቢ ነው ማሰር፡፡(ከመጸሃፉ የተወሰደ)

 

 

በጥቂቱ በሚዲያ ስንሰማው የነበረው ኦቲዝም የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ለእነ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ ምስጋና ይግባቸውና ብዙ እንድንገነዘብ አድርጎናል፡፡ ወላጅ የሰው ትችት  ፍራቻ አፉ ተሸብቦ፣ መላው ቢጠፋው ልጁን ሳይወድ በግዱ በር ቆልፎ ድብቆ ለዘመናት ቅስሙ ተሰብሮ የኖረበት ዘመን እያበቃ ነው፡፡ በአገራችን ምሁራን ስለኦቲዝም ግዜን ጠብቆ በሚዲያ ከሚሰጡት ቃለመጠይቅ ባለፈ የተጻፈ ባይኖርም ይህን ፈር ቀዳጅ መጸሃፍ “አይኔን ተመልከተኝ”ን እነሆ ላሉን ለዶ/ር ዮናስ ባህረጥበብም አይናችንን ይከፍተዋል እና ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡

በተለምዶ እኛ ኦቲዝም ስለምንለው የጤና ችግር ሳይንሱ የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር (Autism Spectrum Disorder) ይለዋል፡፡

ኦቲዝም ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ላይ የሚታየው ምልክት ከአንድ ልጅ የሌላው የተለያየ ነው እንደሌላ የጤና ችግር ምልክቱን አይቶና አካልን መርምሮ በሽታው ይሄ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ለዚህም ነው ወላጆች እንደጤና ችግር አይተው በቶሎ የህክምና እርዳታ ለመግኘት የሚዘገዩት፡፡ የህክምና ባለሞያዎችም ከወላጆች ብዙ መረጃዎችን ሰብስበውና ልጁን ሁኔታ ተከታታይ ምልከታ አድርገው የተደራጀ መረጃ ከያዙ በኋላ ነው  ችግሩ ይሄ ነው በዚህ ሁኔታ መረዳት አለበት ሊሉ የሚችሉት፡፡

የኦቲዝም የአይምሮ እድገት መዛባት ሲባል እኛ እንደምናስበው የአይምሮ ብስለት ችግር ብቻ ሳይሆን የአይምሮ ብስለት ደረጃቸው (ስእል፣ ሂሳብና በኤሌክትሮኒክስ) የላቀና የረቀቀም ሊሆን ይችላል፡፡

በአለም ላይ የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ከሰማንያ ስምንት ልጆች ውስጥ አንድ ልጅ ላይ ይታያል፡፡በአፍሪካም ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት (እኛንም ያጠቃልላል) የተደረገ ጥናት ከመቶ ልጆች ውስጥ 11-33 የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ውስጥ ይኖራሉ፡፡

ከአሜሪካ የወጣ መረጃ የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር በየአመቱ 10-17 በመቶ እያደገ መጥቷል፡፡

በአገራችን የተደራጀ ጥናት ባይኖርም በህክምና  አገልግሎት መስጫዎች የሚመጡ በችግሩ ውስጥ ያሉ ታካሚ ልጆች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እያየን ነው  ይላሉ ዶ/ር ዮናስ ባህረጥበብ፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ እንደ ጆይ፣ ነህሚያና በሃዋሳ ብራይት የኦቲዝም ማእከላትንና የህጻናት ማሳደጊያ ድርጅቶችን ብንጎበኝ የችግሩን ስፋት በጥቂቱም ቢሆን መረዳት ያስችለናል፡፡ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ያሉትን ቤት ይቁጠረው፡፡ ያሉትም ማእከላት አነስተኛ በመሆናቸው ወደ ማእከላቱ ለመግባት ወረፋ የሚጠብቁም ብዙ ናቸው፡፡

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር የፈጣሪ ቁጣ ወይም እርግማን ሳይሆን የነርቭ እና የአንጎል ስርዓት እድገት ችግር ነው፡፡

 

 

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር መንስኤዎች

በዘርፉ ያሉ ተማራማሪዎች እናት በእርግዝና ወቅት ያጋጠማት ህመም፣በወሊድ ግዜ በህጻኑ ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ፣ ህጻኑ ከተወለደም በኋላ በመውደቅ በኢንፌክሽን ወይም በመርዛማ ነገሮች አንጎሉ ከተጎዳ ለኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ተገላጭ ሊሆን ይችላል ከሚል መላምት ውጪ ይሄና ይሄ የችግሩ መንስኤ ነው ብለው ማስቀመጥ አልቻሉም፡፡

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር መንስኤው ይሄ ነው ስለማይባል መከላከል ባይቻልም

  • በእርግዝና ወቅት ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ
  • በተቻለ መጠን በጤና ጣቢያ ወይም በሆስፒታል መውለድ እና
  • ከተወለደም በኋላ ጭንቅላት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችና ኢፌክሽኖችን በመከላከል

ተጋላጭነትን መቀነስ ያቻላል፡፡

 

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ያለበትን ልጅ እንዴት መለየት ይቻላል?

የልጆችን እድገት የምንገመግምበት ዘዴ ቢኖረንም ለማነጻጸር እንዲረዳን የሚከተሉትን የእድገት ደረጃዎች እንመልከት

በአንድ አመቱ

የተስተካከለ እድገት ያለው ለጅ፡ ስሙ ሲጠራ ይዞራል

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ያለበት፡ ስሙ ሲጠራ ምላሽ አይሰጥም ግን ሌሎች ድምጾች ላይ ምላሽ ይሰጣል፡፡

በ1ዓመት ከስድስት ወር፡

የተስተካከለ እድገት ያለው ልጅ፡ መናገር ቢያቅተውም በአካላዊ እንቅስቃሴ ስሜቱን መግለጽ ይችላል

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ያለበት፡አፍ ባይፈታም ሌላ ዘዴ በመጠቀም ለመግበባት ሙከራ አያደርግም

  • ንግግሩም በቴሌቪዝን ያየውን ወይም ሰዎች ሲሉ የሰማውን ደጋግሞ ከማለት ያላላፈ ነው
  • አፍ መፍቻው ባልሆነ እና በማይገባ ድምጽ ሊግባባ ይሞክል

በሁለት ዓመት

የተስተካከለ እድገት ያለው ልጅ፡ የወደደውን ስእል ወይም መጫወቻ ለወላጆቹ ያሳያል ስሜቱንም ያጋራል

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ያለበት በሞባይል ስልክ ለመጫወት ሲፈልግ እንዲከፍቱለት እርዳታ ይጠይቃል

  • ጨዋታውንም ሆነ ደስታውን ከሰው ጋር የመጋራት ፍላጎት አያሳይም
  • የወላቹን ፊትም አይመለከትም፡፡

የተስተካካለ እድገት ያላቸው ልጆች የአካባቢ ለውጥን ባይፈልጉም ከለውጡ ጋር ተስማምተው ለመኖር ይሞክራሉ

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ውስጥ ያሉ ልጆች ለውጥን አምርረው ይጠላሉ፡፡

የሚወዱት አሻንጉሊት  ጨዋታ ወይም ሙዚቃ ዘፈን…ኖራቸዋል

ለሚወዱት ነገር ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ

በጣም ሚወዱት ግኡዝ ነገር ይኖራቸዋል

የማህበራዊ ግንኙነት ክህሎታቸው በጣም ዝቅተኛ ነው

በሚያወሩበት ወቅት የሰው አይን ማየት ያቅታቸዋል

ለምሳሌ እንደ ልደት በመሰሉ ልጆች የሚበዙበት ቦታዎች ላይ ከልጆች ጋር ከመጫወት ይልቅ መጫወቻ ይዘው ብቻቸውን ይቀመጣሉ (ሰው ይልቅ ከግኡዝ ነገሮች ጋር ማሳለፍ ያዘወትራሉ)

ለሌላ ሰው ትርጉም የማይሰጡ እንቅስቃሴ ጋር ለረጅም ግዜ ይቆያሉ

ነገሮች ሁል ግዜ አንድ አይነት እንዲሆኑላቸው አጥብቀው ይፈልጋሉ፡፡ ጥላቻቸውንም በባህሪ ለውጥ ይገልጻሉ፡፡

በጠቅላላ የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ውስጥ ያሉ ልጆችን ለመለየት የሚያስችሉ ሶስት መለያ ታላላቅ ምልክቶች እንዳሉ የዘርፉ ሙያተኞች ያስቀምጣሉ፡፡

ማህበራዊ 

  • በብዛት አይንን ማሸሽ የአይን ለአይን ግንኙነት አለመኖር ሰው ሰላም ሲሉም ፊትን ዙሮ እጅን መዘርጋት
  • የሰውነት እንቅስቃሴን በመጠቀም ወይም የፊትን ገጽታ በመለዋወጥ ሰዎች ጋር መግባባት አለመቻል ከእድሜ እኩያ ከሆኑ ልጆች ጋር ለመጫወት መቸገር
  • የሌሎችን ስሜት አለመረዳት/አለመገነንዘብ
  • ከሰው ይልቅ ከግኡዝ ነገሮች ጋር የበለጠ ግዜ ማሳለፍ
  • ፍላጎታቸውን ለሌሎች መጋራት አለመፈለግ

ተግባቦት

  • በወቅቱ አፍ መፍታት አለመቻል ወይም መዘግየት
  • ያልተለመዱ ንግግር ወይም ትርጉም የሌላቸውን ቃላት ማውጣት
  • ንግግራቸው ተለዋዋጭ አለመሆን መልሰው መልሰው አንድ ነገር ከቴሌዥን የሰሙት ወይም የሚያውቁት ብቻ መናገር
  • ነገሮችን መደጋገም
  • እንደ ልጅ ሎሎች የሚያደጉትትን ለመቅዳት/አስመስሎ ለመጫወት አለመፈለግ
  • ራስን በስም /በተወላጠ ስም መጠወራት
  • ከሌሎች ጋር መግባባት መቸገር

ተደገጋሚ ባህሪን ማየት

  • ድርጊቶቸ ወይም እንቅስቃሴዎችን መደጋጋም(ጣትን ማራገፍ እጅን ማራገብ፣ መወዛወዝ፣ መሽከርከር እጅን መንከስ)
  • ያልተለመደ፣ ብርቱ፣ የተገደበ ፍላጎቶች ማሳየትና ብዙ ግዜ ስለ ተመሳሳይ ርእስ ማውራት በተመሳሳይ ነገሮች መጫወት ስለ አንድ ጉዳይ ብዙ ማወቅ (ዘፈን ሞባይል መክፈትና ቻናሎችን ጌሞችን መለየት)
  • በአሻንጉሊት የተለያየ ክፍሉ እንጂ በሙሉ አካሉ አለመጫወት መኪናም ከሆነ ጎማው ላይ ብቻ ማተኮር

 

 

  • ፍላጎታቸው በጣም የተገደበ በመሆኑ በአንድ ነገር/  ላይ ብቻ ከሚገባው በላይ መመሰጥ/ በአብዛኛው በአንድ ቁስ ላይ በቻ ግዜ ማጥፋት
  • አንድ ዘፈን ወይም መዝሙር ወይም ሌላ ነገር መደጋገም

እነኚህን የሶስትዮሽ ማእዘን ምልክቶችን ልጆት ላይ ካስተዋሉ የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር እንዳለበት አመላካች ነውና በህክምና ማረጋገጥ ይጠበቃል፡፡

ውጤቱ ለየትኛውም ወላጅ ቢሆን አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል ግን መረጋጋትና ሃቁን ተቀብሎ መፍትሄዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ውስጥ ያሉ ልጆች ሁሉም ባይሆኑም  እንደ

  • ትኩረት ማጣትና መቅበጥበጥ
  • ድብርት
  • ዳውን ሲንድሮም
  • የጨጓራና የአንጀት
  • የአይምሮ እድገት ብስለት ችግር

ተጓዳኝ የጤና ችግሮችም ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡

ለኦቲዝም ሙሉ በሙሉ የሚፈውስ ህክምና ባይኖርም ተያይዘው የሚመጡትን ጉድለቶች በህክምና እና በትምህርት ማስተካከል ይቻላል፡፡

 

በሃገራችንም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በመቀሌ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ሪፈራል ሆስፒታል፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል፣ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል  የአእምሮ ህክምና ክፍሎች ውስጥ አገልግሎት ማግኘት ይቻላል፡

የኦትዝም  ችግር ልጁ ላይ ዘርፈብዙ ጫና ስለሚያሳድር የሚሰጠው  እርዳታም እንዲሁ

  • የስነልቦና ባለሞያ
  • የአእምሮ ሃኪም
  • የንግግር ህክምና ባለሞያ
  • የልዩ ፍላጎት አስተማሪና የማህበራዊ  አገልግሎት ባለሞያዎችን እገዛ ይጠይቃል፡፡

ከምንም በላይ በመስኩ የሰለጠኑ የህክምና ባለሞያዎች፣  በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶችን የአካቶ ትምህርት መርሃ ግብር ማስጀመር፣ ስለ ኦቲዝም ለመምህራን ሥልጠና መስጠት፣ የኦቲዝም ማእከላት ማስፋፋትና መገናኛ ብዙሃንም ለህብረተሰቡ ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ቢሰሩ የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ይላሉ ዶ/ር ዮናስ በመጸሃፋቸው፡፡ እኔ ይሄን ያህል ካልኩ

  • ኦቲዝም ችግርና ተደባዳቢነት
  • የኦቲዝም ችግርና የሚጥል በሽታ
  • የኦቲዝም ችግርና እንቅልፍ እጦት
  • ቤተሰብ ውስጥ አንድ ልጅ በኦቲዝም ችግር ውስጥ ሲኖር ምን መደረግ አለበት?
  • ወዳጅ ዘመድ የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር ውስጥ ያሉ ልጅ ያለውን ቤተሰብ እንዴት ሊረዳ ይችላል ምንስ ከማድረግ መቆጠብ አለበት?

የኦቲዝም ህብር የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር እና የመዳን ተስፋው ምን ያህል ነው የሚለውንና ሌሎች በጣም ጠቃሚ ግንዛቤና እውቀትን ሊለግሱ የሚችሉ ሃሳቦች የተካተተበትን መጸሃፍ እስቲ ያንብቡት ለሌሎችም ያጋሩ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe