አንጋፋውና የመጀመሪያው የኢትዮጽያ ዩኒቨርሲቲ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75 ዓመት ሞላው፡፡ በእነዚሁ ዓመታትም የውጭ ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ280ሺ በላይ ምሩቃንን አስመርቋልም ተብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 75ኛ ዓመቱን የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ሁነቶች እስከ መጭው ዓመት ታህሳስ ወር ድረስ እያከበረ እንደሚዝቅም ይፋ አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደር ሂደትና የ75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ በዓሉን ለማክበር በሰጠው መግለጫ ነው ይህ የተሰማው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዜዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው የኢትዮጽያ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ከተመሠረተ 75 ዓመት ሞላው ብለዋል፡፡
በዓሉንም ያለፈውን በመዘከር ፤መጭውን በማለም በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በእነዚህ ዓመታት የማስተማር ሂደት ውስጥ በኢትዮጽያ እና በአፍሪካ መሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾችን ማበርከት የቻለ እንደሆነም ተገልጻል፡፡ ከ280ሺ በላይ ምሩቃንንም አስመርቋል፡፡
ለወራት ያክል ይዘልቃል የተባለው የበዓሉ አከባበርም፡የምርምር ኮንፍራንሶች፡የስፖረት ውድድሮች፡የኪነ ጥበብ ስራዎች የሚቀርቡበት እንዲሁም የቀድሞ ምሩቃን ሳምንት በሚል የተለያዩ ዝግጅቶች ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ራስገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲወጣ በተወሰነው መሠረት መልሶ ተደራጅቶ ወደ ስራ እንደገባም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

