ኢራናዊያን ሳይንቲስቶች በሚስጥር ወደ ሩሲያ ተጉዘው እንደነበረ ተሰማ፡፡ እነዚሁ ኢራናዊያን የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ሁለት ሚስጥራዊ ስብሰባዎችን በሞስኮ ባለፈው ዓመት እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
ይህንን ግንኙነት መሠረት አድርጎም ኢራን አሁን በሩሲያ ድጋፍ አማካኝነት የኒውክሌር ግንባታዋን እያከናወነች ነው ወይ የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡
ኢራናዊያን ሳይንቲስቶቹ ሚስጥሯዊ ጉብኝቱን ያደረጉት ባለፈው ዓመት 2024 እንደሆነ የፋይናሻል ታይምስ ዘገባ ያስረዳል፡፡ ይሄው ድብቅ ጉዞም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም በቴክኖሎጂና በሌሎች ጉዳዮችም ለማገዝ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በድብቅ ከተጓዙት ውስጥ ከሦስት የኢራን ዩኒቨርሲቲዎች የተመለመሉ ሳይንቲስቶች እንደነበሩም ተነግሯል፡፡
እነዚሁ ሳይንቲስቶች ሁሉም ወደ ሩሲያ እንዲጓዙ የተደረገው በዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንደነበረም መገለጹ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ዓመት የኒውክሌር ሳይንቲስቶቹ በሩሲያ የወታደራዊ ላብራቶሪ ተገኝተው እንደነበር ከዚህ ቀደም በወጡ መረጃዎች ተገልጻል፡፡
ሁለቱም ሚስጥራዊ የሳይንቲስቶቹ ጉዞዎች ከካሜራም ይሁን ከህዝብ እይታ የተሰወሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በርግጥ ኢራን በዚህ ስዓት ሙሉ በሙሉ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ዩራኒየም እየበለጸገ እንዳልሆነ ገልጻለች፡፡ ምክንያቱም በሰኔው ጦርነት ወቅት በደረሰባት ጉዳት እንደሆነም አስታውቃለች፡፡
ነገር ግን ለሰላማዊ አገልግሎት ለሚውል አላማ ዩራኒየም እንዲበለጽግ ከማድረግ ማንም ሊያስቆማት እንደማይችል ትገልጻለች፡፡ ስለሆነም ዩራኒየም ማበልጸጓን እንደምትገፋበት አስታውቃለች፡፡
በዚህ ወቅት ቴህራን ከእስራኤል ጋር ዳግም ጦርነት ይነሳል በሚል ሙሉ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች በመግለጽ ላይ ነች፡፡ የሚሳኤል አቅሟን በብዙ እጥፍ እያሳደገችው እንደሆነም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎችም ባለስልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺም በኒውክሌር ፕሮግራማችን ዙሪያ የምንሰጠው እጅ አይኖረም በማለት ጠንከር ያለ ንግግር በተደጋጋሚ ያሰማሉ፡፡//
የእስራኤል ጦር 17 የሚሆኑ የሃማስ ሰዎችን መግደሉንና በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ 17 የሃማስ ታጣቂዎችን መግደሉን እንዲሁም በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ የተደረሰውን ተኩስ የማቆም ስምምነት እንዲጣስ በማድረግ ላይ የነበሩ ስለመሆናቸውም ተነግሯል፡፡
ጦሩ ባደረገው ዘመቻም አስራአንዱን የሃማስ ታጣቂዎች የገደለ ሲሆን፤ስድስቱን ደግሞ በቁጥጥር እንዳዋለ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
እነዚሁ የሃማስ ሰዎች በቡድኑ የምድር ውስጥ ምሽጎች በደቡባዊ የጋዛ ክፍል ነው በጦሩ እርምጃ የተወሰደባቸው፡፡
እነዚሁ የቡድኑ ሰዎች በምድር ውስጥ አድርገው የእስራኤል ጦር ወደሚገኝበትና ቢጫ መስምር ወደተሰመረበት ስፍራ ለመግባት ሲሞክሩ የተያዙ እንደሆኑም ጦሩ አስታውቋል፡፡
በጦሩ ከተገደሉት የቡድኑ ሰዎች መካከል አንደኛው ነባር የቡድኑ የጦር መሳሪያ ማምረቻ አመራር እንደሚገኝበትም ይፋ ሆኗል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትንያሁ ጽ/ቤት ክስተቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የጣሰ ነው ብሎ፤እስራኤል አሁንም ስምምነቱን ለማክበር ያላትን ቁርጠኝነት ገልጻል፡፡
እስራኤል ሃማስ ቀሪ ያልተመለሱ አስክሬኖችን እንዲመልስ፡ትጥቁን እንዲፈታ ትፈልጋለች፡፡ ሃማስ ለአደራዳሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዳልጠሰ እንዲጣስም የምታደርገው እስራኤል እንደሆነች ይገልጻል፡፡//

