ከሁለት ወራት በላይ ያስቆጠረውን ጦርነት ሊያስቆም ይችላል የሚል ምላሽ ከቴህራን በኩል ይሰማል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ይህ ግን ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት አሜሪካ ላቀረበችው ምክረ ሀሳብ የሰጠችውን ምላሽ ውድቅ አድርገዋል፡፡
ኢራን ይህንን ምላሻን ለዋሽንግተን በአስታራቂዋ ፓኪስታን በኩል የላከች ሲሆን ትራምፕ ግን እንደማይቀበሉት ይፋ አድርገዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ የተሰጠው ምላሽ ተቀባይነት የሌለው ነው ከማለት ውጪ የትኛው የኢራን ቅድመ ሁኔታ ወደዚህ እንዳመራቸው ግን በዝርዝር ያሉት ነገር የለም፡፡
ኢራን በበኩሏ ጦርነቱን ለማጠናቀቅ ያግዛል ያላችውን ምላሻን ሰጥታለች፤ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደዱት አልወደዱት፤ግድ የላትም የሚሉ አስተያየቶች ከቴህራን ፖለቲከኞች በኩል ተሰምቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ ኢራን እኛ በተስማማንበት ነጥብ ከተስማማች ይጠናቃቃል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ዋሽንግተን ዳግም ጥቃቷን አጠናክራ ትቀጥላለች በማለት ማስጠንቀቃቸው እንዲሁ አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ሚዲያ ባጋሩት መልዕክት ከኢራን የተላከውን ምላሽ አይቸዋለሁ፤አልወደድኩትም በፍጹም ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ቴህራን ለአሜሪካው እቅድ የሰጠችው ምላሽ በርካታ ቁልፍ ነገሮችን እና ቅድመ ሁኔታዎችን መያዙ ተሰምቷል፡፡
ኢራን ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ያሉ ጦርነቶች እንዲቆሙ፡በጦርነቱ ለደረሰው ኪሳራ ሙሉ ካሳ እንዲከፈላት፡ዳግም ጥቃት እንደማይከፈትባት ዋስትና እንዲሰጣት እና ማዕቀቦች እንዲነሱላት ጠይቃለች መባሉን የኢራን መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ በወደቦቿ ላይ የጣለችውን እገዳ ማንሳት እንደሚኖርባትም ጠይቃለች ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ጋር በዚህ ሳምንት በቻይና በሚኖራቸው ንግግር ስለ ኢራን ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዋሽንግተን ቻይና ቴህራን ወደ ስምምነት ጠረጼዛው እንድትመጣ ግፊት ታደርጋለች የሚል እምነት አላት፡፡
መሪዎቹ በንግግራቸው ከኢራን በተጨማሪ ስለ ታይዋን ጉዳይም ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንደ አሜሪካ ባለስለጣናት መረጃ የትራምፕ የሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝት በዚህ ሳምንት ይደረጋል፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ድርድር ወይም ንግግር እጅ የመስጠት ምልክት አይደለም፤ማንኛውም ንግግር የሀገራችንን ጥቅም የሚያስከብር በሆነበት አግባብ ብቻ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢራን ጦር ቃል አቀባይ ጠላቶቻችን እንዳለፈው ስህተታቸው ለሌላ ዙር ጥቃት ከተዘጋጁ ያልጠበቁት ይገጥማቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡//

