በኢስላማ ባድ የሚጀመረው ድርድር ጥሩ ውጤት የማያመጣ ከሆነ ዳግም ወደ ጦርነት ይገባል የተባለው፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላለፉት ስድስት ሳምንታት ያህል ዘልቆ የነበረውን ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት እንዲበርድ አድርገውታል፡፡ አሜሪካ የኢራንን የሃይል መሠረተ ልማቶች እና ድልድዮችን የምታጠቃበትን የጊዜ ገደብ ለሁለት ሳምንት ያህል አራዝመዋለች፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ አሜሪካ እንዳስጠነቀቀችው እንደምታደርግ ነው ትራምፕ ያስታወቁት፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ኢራንን ወደ አሁኑ ስምምነት እንድትመጣ በማድረጉ ሂደት ቤጂንግ ግፊት እንዳደረገች ነው ያነሱት፡፡
ቴህራን የተደረውን የሁለትዮሽ የተኩስ አቁም ስምምነትን መሠረት በማድረግ የንግድ መርከቦች በኢራን የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር እየተደረገባቸው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዲተላለፉ እንደምትፈቅድ ይፋ አድርጋለች፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ኢራን ለጊዚያዊት የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ታደርጋለች ብለዋል፡፡
ኢራን አቅርበዋለች በተባለው ባለ 10 ነጥብ የሰላም እቅድ ውስጥ የአሜሪካ ጦር ከቀጠናው ሙሉ በሙሉ እንዲለቅ እና ማዕቀቦች እንዲነሱላት የሚጠይቅ መሆኑን ሪፖርቶች አመላክተዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕም በኢራን በኩል የቀረቡት 10 ነጥቦች ለድርድር ጥሩ መነሻዎች ናቸው በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ምንም እንኳን አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈራረሙም በገልፍ ሀገራት ላይ ግን ዛሬም ጥቃቶች ቀጥለዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ እና ኢራን ከነገ በስቲያ አርብ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ ይሄው ንግግርም አሁን የተደረሰው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ዘላቂ ስምምነት ያመራ እንደሆነ ለማየት ነው፡፡
ኢራን ንግግር ይደረጋል ማለት ጦርነቱ አብቅቷል ማለት አይደለም አሁን ሰላም ሰፍኗል ሳይሆን ጦርነቱ ባለበት እንዲቆም ሆኗል ማለት ነው ብላለች፡፡ የኢራን መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው ንግግሮች ካልተሳኩ አሁንም ጦርነቱ ዳግም ይጀመራል የሚል ይዘት ያላቸውን ዘገባዎችን ይዘው ወጥተዋል፡፡
ኢራን በቀጣይ ቀናት ከአሜሪካ ጋር የሚደረጉ ንግግሮች ካልተሳኩ ዳግም ወደ ጦርነቱ እንገባለን አለች

