ኢራን ዛሬ በኢስላማባድ ይደረጋል በተባለው ድርድር ላይ ተደራዳሪዎቿን እንደማትልክ ገለጸች

ኢራን ዛሬ በኢስላማባድ ይደረጋል በተባለው ሁለተኛው ዙር ድርድር ላይ ተደራዳሪዎቿን እንደማትልክ ገለጸች፡፡

ቴህራን አሜሪካ የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት ገና ከጅምሩ ስትጥስ ቆይታለችና ከእርሷ ጋር ለንግግር ለመቀመጥ እቸገራለሁ ስትል ገልጻለች፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢራን ባለፈው ሰኔ ወር አሜሪካ በድርድር መሃል ላይ ጥቃት መክፈቷን አንረሳውም ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትላንት እሁድ በሰጡት መገለጫ የአሜሪካ ተደራዳሪ ሉዑካን ወደ ፓኪስታን ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ ዊትኮቭ እና ኩሸነር በቅድሚያ ወደ ኢስላማባድ ይጓዛሉ የተባለ ሲሆን፤ምክትል ፕሬዝዳንት ጂዲቫንስ ንግግሩ ከተጀመረ በኋላ እንደሚቀላቀሉ ነበር የተገለጸው፡፡

ቴህራን ከዋሽንግትን ጋር ዛሬ ይደረጋል ተብሎ በታቀደው ሁለተኛው ዙር ድርድር ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላት መግለጻ እየተነሳ ነው፡፡ በሀገራቱ መካከል ስምምነት ካልተደረሰ ጦርነቱ ዳግም ተባብሶ የሚቀጥልበት እድል እንዳለ ተመላክቷል፡፡

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባግሄ በአሜሪካ ዲፕሎማሲ ላይ እምነት እንደሌላቸው ገልጻል፡፡

ቃል አቀባዩ አሜሪካ የተደረሰውን ተኩስ አቁም እየጣሰች ባለችበት ሁኔታ እንዴት አድርገን አምነናት ለንግግር ዳግም እንቀመጣለን ብለዋል፡፡ ቃል አቀባዩ አክለውም የኢራን የድርድር ሁኔታ የሚመራው በብሔራዊ ጥቅም ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ ገደባችን ብሔራዊ ጥቅማችን ነው ይበሉ እንጂ የድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎችን በዝርዝር አልገለጹም፡፡

ምንም እንኳን ቃል አቀባዩ ስለ ድርድሩ ይህንን ቢሉም፤ኢብራሂም አዚዝ የተባሉ የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደህንነት ኮሚቴ አባል ግን ከዚህ የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሰውየው በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ያለው ሁለተኛው ዙር ንግግር ኢራን ያስቀመጠችውን ቀይ መስመር በተከተለ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አስታራቂዋ ፓኪስታን የሀገራቱ ዳግም ድርድር እንዲቀጥልና ነገሮች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው የማድረግ ጥረቷን ስለመቀጠሏ እየተነገረ ነው፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ  የኢራኑ ፕሬዝዳንት መስድ ፔዜሽኪያን ከአሜሪካ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ ዲፕሎማሲ መፍትሔ ቢሆንም፤አሜሪካን ግን ማመን እጅግ ከባድ ነው አሉ፡፡

በቴህራን እና በዋሽንግተን መካካል የተፈረመው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በይፋ የፊታችን ዕረቡ ይጠናቀቃል፡፡

ይሄው ስምምነት ከመጠናቀቁ በፊት ሁለተኛውን ዙር ድርድር በፓኪስታኗ መዲና ኢስላማባድ ለማድረግ ዩናይትድ ስቴትስ ዛሬ ተደራዳሪዎቿን የምትልክ ሲሆን፤ኢራን ግን እስካሁን በድርድሩ ላይ እንደማትሳተፍ ነው እየተሰማ የሚገኘው፡፡

የኢራን መንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያ ምንጮች ነገሩኝ ብሎ ባወጣው ዘገባ ኢራን ሁለተኛውን ዙር ድርድር ከአሜሪካ ጋር የማድረግ ፍላጎት የላትም ብሏል፡፡

ኢራን ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በአሜሪካ ቅጥ ባጣ ፍላጎት እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጻል፡፡ አሜሪካም ሆነች ኢራን የተደረሰውን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ እርስ በርስ እየተካሰሱ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ኢራንን ተጠያቂ የማድረግ ጨዋታዋን ቀጥላለች ስትል ኢራን ገልጻለች፡፡

ይህ የአሜሪካ ጨዋታ አሜሪካ ጥሩ የሚባል ሚና እየተጫወተች መሆኗን ለማሳየት ያለመ ስለመሆኑ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጻል፡፡ በዚህ የተነሳ ዋሽንግተን ለሃቀኛ ድርድር ፍላጎት የላትም ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe