የአፍሪካ አገሮች ከኮታና ከቀረጥ ነፃ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዲልኩ ከሚፈቅደው የአጎዋ ስምምነት ውጪ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ያማከለ አዲስ የታሪፍ ስምምነት ማዕቀፍ በማድረግ፣ ከቀረጥ ነፃ ኤክስፖርት ታደርጋቸው የነበሩትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ለመላክ ከአሜሪካ ጋር ድርድር እንደምታደርግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በሚኒስቴሩ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ንግድ ትስስር ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን አበራ፣ ድርድሩ የሚደረገው አሜሪካ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ወደ አገሯ በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለችውን የአሥር በመቶ ታሪፍ አስመልክቶ በቀጣይ በሚደረግ ውይይት እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ መላክ የሚቻልበት ዕድል መነሳቱን የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹በአጎዋ ምክንያት ያጣናቸውን ጥቅሞች በዚህ ማዕቀፍ ሥር ለድርድር በማቅረብ፣ ምርቶችን መላክና አገራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ድርድር ውስጥ እንገባለን፤›› ብለዋል። ሆኖም ድርድሩ መቼ እንደሚጀመር እስካሁን የተቆረጠ ቀን እንደሌለ የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል የተሰረዘችው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በመንግሥትና በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት በተፈጠሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት እንደሆነ ይታወሳል፡፡
የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግና ሥራ ይፈጥራል በሚል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሮች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኘ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና የታሪፍ ጭማሪ ይደረግባቸዋል ተብለው በተመረጡ ሌሎች ዘርፎች ላይ አሜሪካ ያላትን ፍላጎት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በደብዳቤ ማሳወቋን የጠቀሱት አቶ ዘሪሁን፣ የኢትዮጵያ ፍላጎትና ጥቅምን በማስጠበቅ ጭማሪው እንዴት ተፈጻሚ ይሆናል በሚለው ላይ የዝግጅት ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል። ‹‹የአሥር በመቶ የታሪፍ ጭማሪው በአሜሪካ ፍላጎት ብቻ የሚሆን አይደለም፤›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ሁለቱ አገሮች በዚህ ላይ ሰነዳቸውን አቅርበው የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ድርድር ከተደረገ በኋላ እንጂ፣ በአንዴ የሚጨመር ታሪፍ የለም፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያም በኩል ይህንን የተመለከተ ሰነድ ተዘጋጅቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ወደ አሜሪካ እንደሚላክ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምርቶች ላይ የምትጥለው የጉምሩክ ቀረጥ ከዜሮ እስከ 35 በመቶ መሆኑን ያወሱት አቶ ዘሪሁን፣ አማካዩ 14.5 አካባቢ በመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹አሜሪካ የጣለችው የአሥር በመቶ ታሪፍ አማካዩን እንደ አጠቃላይ ወደ አሥር በመቶ እንዲወርድ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ምርት ተለይቶ የኢትዮጵያን ጥቅምን በማስከበር ታሪፉ እንዲወሰን ስትራቴጂካዊ ድርድር ይደረጋል፤›› ሲሉ አክለዋል።
የአሥር በመቶ ጭማሪው በየትኞቹ ምርቶች ላይ ይሆናል? ምን ዓይነት ጥቅምና ጉዳትስ ይኖረዋል? በሚለው ላይ፣ ኢትዮጵያ የራሷን ፍላጎት በድርድሩ ላይ እንደምታንፀባርቅም ተናግረዋል።
የአሥር በመቶ የታሪፍ ጭማሪው እንዳይደረግባቸው ለድርድር የሚቀርቡ ምርቶች የትኞቹ ላይ እንደሆነ በግልጽ የታወቀ ነገር አለ ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ዘሪሁን፣ አሁን እንደማይታወቅና በዚህና አጠቃላይ የድርድሩ ሁኔታ ላይ ከተለያዩ የሚኒስቴር መሥርያ ቤቶች ጋር ውይይት እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡(Reporter News)

