ኢትዮ ቴሌኮም ስማርት ጅግጅጋ ፕሮጀክትን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ጋር ተፈራረመ

ኩባንያው ለማሕበረሰቡ የዘመኑን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በፍጥነት በማቅረብ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን በማድረግ የማህበረሰቡን የዕለት ከዕለት አኗኗር ዘይቤ እና የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ እመርታ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡
በተለይም ኩባንያው የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ በማድረግ ለአስተማማኝ ደህንነት፣ ለኑሮ ምቹ፣ ጽዱ እና ጥራት ላለው የከተማ ሕይወት፣ ለኢኮኖሚ ልማትና እድገት፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት እንዲሁም ቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ወደርየለሽ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
ኩባንያው ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐረር፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕና፣ አርባ ምንጭና ቢሾፍቱ ከተሞች ተግባራዊ ያደረገውን የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት በጅግጅጋ ከተማ ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱም ከተማዋን ለማዘመን የሚያስችል የክላውድ፣ የጥሪ ማዕከል፣ የዳታ ሴንተር፣ እጅግ ከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት ያለው ኢንተርኔት፣ የኦፕቲካል ፋይበር እና ሌሎች የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡
የስማርት ሲቲ ፕሮጀክቱን በዋናነት ከ5ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ጋር በማስተሳሰር የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ትራንስፖርት፣ የግብር አሰባሰብ እና እንደ ቱሪዝም ያሉ አገልግሎቶችን ከማዘመን ባሻገር ደኅንነቷ አስተማማኝ የሆነች የጅግጅጋ ከተማን ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሁሉንአቀፍ የዲጂታል ሶሉሽኖችን ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባሻገር ክፍያዎችን በቴሌብር በቀላሉ በማስፈጸም ውጤታማነትን በእጅጉ ለማሳደግ የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም ተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንዲችሉ በማገዝ ሕይወታቸውን ቀላል ለማድረግ እና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለመቀየር ቁልፍ ሚና ይኖረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኘውን የጅግጅጋ ከተማን ለኢንቨስትመንት መዳረሻነት ምቹ በማድረግ ተወዳዳሪነቷ እንዲጨምር፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ እንዲሁም የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ኢትዮ ቴሌኮም የላከልን ዜና ይጠቁማል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe