ኢትዮ ቴሌኮም ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማሕበረሰባችን ከማስተዋወቅ እና በሰፊው ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ሀገራችን በዲጂታል አገልግሎት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ ያለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የዘመናችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በፍጥነት እያቀረበ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን እያደረገ ይገኛል፡፡
ኩባንያው በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘውን የደንበኞቻችንን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉ፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉ እንዲሁም ዘመኑ ያፈራቸውን አስተማማኝና ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ የቴሌኮም እና ዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በስፋትና በቁርጠኝነት በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሚያስችለውን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥቂት ሀገሮች ብቻ ተግባራዊ የተደረገውን የዓለማችን የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የሆነውን የአምስተኛውን ትውልድ የሞባይል አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር ከተሞች እና አካባቢያቸው ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በዛሬው ዕለትም በደቡብ ሪጂን ሀዋሳ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ጣቢያዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ በከተማዋ አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመረ መሆኑን በታላቅ ደስታ ያበስራል፡፡
በዚህ መሠረት ኩባንያው በሀዋሳ ከተማ፡- ፒያሳ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ሕንጻ አካባቢ፣ በፍቅር ሀይቅ አካባቢ፣ በወልደአማኑኤል ዱባለ አደባባይ፣ በዋንዛ/ የቀድሞው አውቶቡስ መናኸሪያ፣ በቅዱስ ገብርኤል አደባባይ፣ በደቡብ ክልል የፋይናንስ ጽ/ ቤት፣ በቅዱስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እና በኃይሌ ሪዞርት አካባቢዎች የሚገኙ የድርጅት እና ግለሰብ ደንበኞቻችን የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ አድርጓል፡፡ (ኢትዮ ቴሌኮም)

