ኢትዮ ቴሌኮም የፍጥነት መንገዶች ክፍያ በቴክኖሎጂ ለመተካት “ቶሎ” የተሰኘው አገልግሎት ሥራ አስጀመረ

“ቶሎ” (TOLO) የተሰኘ አዲስ የዲጂታል ክፍያ አማራጭ ሥራ ጀመረ; የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር “ቶሎ” (TOLO) የተሰኘውን አዲስ የዲጂታል ክፍያ አማራጭ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል

ቀደም ሲል በእጅ ንክኪና በጥሬ ገንዘብ ሲከናወን የነበረውን የፍጥነት መንገዶች ክፍያ በቴክኖሎጂ ለመተካት “ቶሎ” የተሰኘው አገልግሎት ሥራ ጀምሯል። ይህ አሠራር “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይን ለማሳካትና የትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ትልቅ እመርታ መሆኑ ተገልጿል። የአገልግሎቱ መጀመር አሽከርካሪዎች የቴሌብር (telebirr) ሱፐር አፕን በመጠቀም ያለምንም ንክኪና እንግልት ክፍያቸውን በሰከንዶች ውስጥ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፣ ተቋማቸው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የፋይበር መሠረተ ልማቶችን በስፋት እያበለጸገ ይገኛል። ዛሬ የተጀመረው የዲጂታል ክፍያ መርሃ ግብር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚያሳልጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል በበኩላቸው፣ በ2017 በጀት ዓመት 2.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስመዘገበው ተቋሙ፤ በ2018 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ብቻ 1.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል። ኢንተርፕራይዙ በቀን ከ32 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ፣ አዲሱ የ”ቶሎ” ዲጂታል ክፍያ አሠራር ጊዜን ከመቆጠብ ባሻገር የአገልግሎት ጥራትንና የመንገድ ደኅንነት ቁጥጥርን እንደሚያሳድግ አቶ ሙስጠፋ አክለዋል። አዲሱን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የሚጠቀሙ ደንበኞችን ለማበረታታት የ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ይህ ማበረታቻ ደንበኞች ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ወጥተው ወደ ዘመናዊው አሠራር እንዲቀላቀሉ የሚያግዝ መሆኑ ተነስቷል። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር የሚገኘው ይህ ተቋም፣ አገልግሎቱን 100 በመቶ ዲጂታል ለማድረግና አረንጓዴ ኢነርጂን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe