ኢትዮ ቴሌኮም የ2017 በጀት ዓመት 162 ቢልየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ገቢው የእቅዱን 99 በመቶ የሸፈነ ነው። ከዚህ ገቢ ውስጥ 76 ቢልየን ብር ያልተጣራ ትርፍ መሆኑን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በሳይንስ ሙዚየም በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት ኢትዮ ቴሌኮም በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይኸን እጅግ የላቀና የሚያኮራ ውጤት በማምጣቱ ለኩባንያው ማኔጅመንትና ሰራተኞች እንዲሁም አጋሮች በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
በበጀት አመቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ72 ነጥብ 9 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ 193 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ሲሆን የእቅዱን 101 ነጥብ 8 በመቶ አሳክቷል፡፡
ኩባንያው ካገኘው ገቢ 43 ነጥብ 76 ቢልየን ብር የታክስ ግዴታውን ተወጥቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም ያገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 28.6% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 22.7%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 12.9%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ7.6%፣ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሽያጭ 5.4%፣ የመሰረተ ልማት ኪራይ 2.2%፣ ቴሌብር 2.7%፣ ኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን 6.2%፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 11.7% ድርሻ አላቸው፡፡
በበጀት ዓመቱ 2.38 ትሪሊዮን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በቴሌብር በማከናወን የእቅዱን 116.9% ያሳካ ሲሆን አጠቃላይ አመታዊ የግብይት መጠኑ (Transaction Volume) 1.06 ቢሊዮን ነው፡፡ አገልግሎቱ ከተጀመረ ጀምሮ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ 4.93 ትሪሊየን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ የአራት አመታት የግብይት መጠኑ 1.98 ቢሊዮን ነው፡፡
የቴሌብር የደንበኞች አጠቃላይ ዓመታዊ የግብይት ዋጋ 1.66 ትሪሊዮን ብር መሆኑን ያሳያል። ከዚህ ውስጥ፣ ከባንክ ወደ ቴሌብር ማስተላለፍ፣ የጅምላ ክፍያዎች እና በዓለም አቀፍ የሓዋላ አገልግሎቶች የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች ያሉ ዲጂታል ገቢዎች (Digital In) 27.1% ድርሻ ሲኖራቸው፤ ከቴሌብር ወደ ባንክ ማስተላለፍ፣ የአየር ሰዓት መሙላት እና የፍጆታ ክፍያዎች ያሉ ዲጂታል ወጪዎች (Digital Out) 18.9% ይይዛሉ። ለነጋዴ የሚከፈሉ ክፍያዎች እና እርስ በእርስ የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች (P2P) የመሳሰሉ የገንዘብ ዝውውሮች (Circulating) ደግሞ 35.8% ድርሻ አላቸው።
በአጠቃላይ በLEAD የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ዘመን 331.5 ቢሊየን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህም ገቢ ከBRIDGE ስትራቴጂ ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ100% እድገት አለው፡፡ ባለፉት ሦስት አመታት ለገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉት ስትራቴጂክ እርምጃዎች መካከል የቴሌብር ፋይናንሻል አገልግሎት መጀመሩ፣ የናሽናል ኢንተርኮኔክሽን ትራፊክ መጨመሩ፣ የመሰረተ ልማት ማከራየት፣ ከ900 በላይ የሞባይል ጣቢያዎች መልሶ በማቋቋም ወደ ስራ መግባታቸው፣ ወደ አገር ውስጥ የተደረጉ የዓለም አቀፍ ጥሪ ገቢ መጨመር፣ የኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን በስፋት መተግበሩ፣ የ4G እና 5G የሞባይል ኔትዎርክ ማስፋፊያ መደረጉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ እና በስትራቴጂ ዘመኑ የተመዘገበው ታላቅ ስኬት የጋራ ርብርብ ውጤት በመሆኑ ለውድ የኩባንያችን ቤተሰብ፤ ለክቡራን ደንበኞቻችን፤ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን ለሆናችሁ አከፋፋዮች፣ አቅራቢዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ለመላው ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋናችን እያቀረብን የጀመርነውን የሃገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አጠናክረን በመቀጠል ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ እናረጋግጣለን ብለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe