ኢትዮ ቴሌኮም 45 ሺህ በላይ መረጃዎችን ያሟሉ እና ከ1,646 መረጃቸውን ያላሟሉ የአክሲዮን ባለቤቶችን ይዞ በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ ተመዘገበ
ኢትዮ ቴሌኮም ወደ አክሲዮን ማኅበር የመቀየር ሂደቱን አጠናቅቆ፣ የኩባንያውን 10 በመቶ ድርሻ የገዙ ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ አክሲዮኖቻቸውን በቀላሉ ማስተላለፍ፣ መሸጥና መግዛት እንዲችሉ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮን ገዝተው የዲጂታል መታወቂያ ያላስተሳሰሩ 1,646 የአክሲዮን ባለቤቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ለእነዚህ ወገኖች ጥሪ እያደረገ እንደሚገኝ የኩባንያዋ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍርሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።
ይህንን ካላደረጉ ግን የአክሲዮን ክፍያቸው ተመላሽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት 45 ሺህ የአክሲዮን ባለቤቶች አስፈላጊውን መረጃ ያሟሉ በመሆኑ በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ መገበያየት እንደሚችሉ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ 248 የውጭ ዜጎች የአክሲዮን ግዥ የፈጸሙ ቢሆንም፣ መረጃቸው ገና እንዳልተሟላ በመጠቆም፣ ገንዘባቸው ተመላሽ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
ከአጠቃላይ የባለአክሲዮኖች የ3.2 ቢሊዮን ብር መዋጮ ውስጥ የ3 ቢሊዮን ብሩ መረጃ ሙሉ በሙሉ የተሟላ መሆኑ ተብራርቷል። የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ፤ መንግሥት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለሕዝብ ለማስተላለፍ የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ፣ ኢትዮ ቴሌኮም የመጀመሪያውንና ዋናውን ምዕራፍ ማሳካቱን ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ላይ በይፋ ለመመዝገብ በርካታ የሕግና የአሠራር ሂደቶችን ሲያከናውን መቆየቱን በመግለጽ፣ ተቋሙን ከነበረበት የመንግሥት የልማት ድርጅትነት በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት ወደ አክሲዮን ማኅበር የማዛወር ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል። በአክሲዮን ባለቤቶች የመረጃ ማጣራት ሥራ ላይም በሰነዱ በተቀመጠው መሠረት ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡ ዝርዝር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡ ተደርጓል።
“የአክሲዮን መደብን ማጽደቅ ቀላል አልነበረም” ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ የቀረቡት መረጃዎች የተሟሉ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ ረዥም ጊዜ ወስዶ ከተሠራበት በኋላ፣ የአክሲዮን መደብ ሥራው ተከናውኖ በኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድ እንዲጸድቅ መደረጉን ገልጸዋል።
“ይህ ሂደት የጋራ ሀብትን ለማፍራትና የጋራ ዕድገትን ለማሳለጥ ታስቦ የተከናወነ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ በአሁኑ ወቅት በአክሲዮን ዝውውር፣ ሽያጭና ግዢ ዙሪያ የተሟሉ መረጃዎች የተሰባሰቡ በመሆኑ በሕጋዊው የባለቤትነት ሥልጣን መሠረት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ይህንን ሂደት ለማጠናቀቅ 11 ወራት የፈጀ መሆኑን ገልጸው፣ በምዝገባው ሂደት ውስጥ የባለሙያ እጥረትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አድካሚ ሥራዎች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻውን የገዙ ባለአክሲዮኖች ድርሻቸውን በቀላሉ ማስተላለፍ፣ መሸጥና መግዛት እንደሚችሉ ይፋ አደረገ
Sourceአዲስ_ማለዳ)

