ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤቢኤች ፓርትነርስ ጋር በመተባበር የሚሰጠው የትምህርት፣ የምርምርና የማኅበረሠብ አገልግሎት እንደሆነ ታውቋል!
ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤቢኤች ፓርትነርስ እ.ኤ.አ ከ2012-2017 በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከ1700 በላይ ባለሙያዎችን በጥራት በማስተማር አራት ደማቅ የምርቃት ሥነ-ሥርዓቶችን አከናውነዋል፡፡
ይህንን አጋርነታቸውን በአዲስ መልክ ለማስጀመርና ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማደስ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውኑም ቆይተዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤቢኤች ፓርትነርስ ጋር በመተባበር የትምህርት፣ የምርምርና የማኅበረሠብ አገልግሎቶችን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
በመሆኑም የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እና የጋራ መግባቢያ ሠነድ የፊርማ ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን መግለጫው የትብብሩን ጠቀሜታ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ያሉትን የአካዳሚ አገልግሎቶች ተደራሽነት መጨመር በሚኖረው ፋይዳ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡
የእነዚህ ተቋማት ስኬታማ ጥምረት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት (Public Private Partnership) በጎ ምሣሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን አጋርነቱም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያሉትን ተፈላጊ የትምህርት መስኮች በይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚረዳው ይታመናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ካሉት ካምፓሶች በተጨማሪ በአዲስ አበባ የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈቱና ያለውን የምርምርና የማኅበረሠብ አገልግሎት ማስፋፋቱ ጥራት ያለው ትምህርት በይበልጥ ለማዳረስ ዕድል ይሰጣል፤ ዩኒቨርሲቲው በልዩነት የሚታወቅበትንና እንደ መርሕ የሚያራምደውን የማኅበረሠብ አገልግሎት ለማስፋፋት የሚያግዝ ይሆናል፤ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የድህረ-ምረቃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ፍላጎት ላላቸው ባለሙያዎች ተጨማሪ አማራጭ መሆን ይችላል፤ እንዲሁም ኤቢኤች ፓርትነስ ካለው የካበተ ልምድ አንጻር ይህንን ፕሮግራም ለመጀመር የጅማ ዩኒቨርሲቲ አጋር መሆኑ ዩኒቨርሲቲው፤ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጥ፣ ተማሪዎች ሙያዊ ቅልጥፍና ባሟሉ ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሒደት ዘመኑ በሚጠይቀው የቴክኖሎጂ እገዛ እንዲያከናወን የሚያስችለው ይሆናል፡፡

