በጮቢ ከተማም ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥትና የግል ንብረት ላይ ውድመት አድርሷል፤
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ በጮቢ ከተማ ሰርጎ በመግባት ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥትና የግል ንብረት ማውደሙ ሲገለፅ በ1868 በአካባቢው ማህበረሰብ እንደተተከለ የሚነገርለትና 146 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን ጥንታዊውን የጮቢ ደብረ መድሃኒት መድኃኒአለም ገዳም ማውደሙም ተነግሯል።
የገዳሙ አገልጋይና ካህን የሆኑት ቄስ ተፈራ ደምሴ እንደገለፁት፣ ሸኔ በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ሰርጎ በመግባት በከተማዋ በርካታ ቤቶችና ተቋማት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ይህን ጥንታዊ ገዳም አውድሟል ብለዋል።
ቡልቶ ቱሬ ተብለው በሚታወቁት የአካባቢው አባት የተቋቋመው ይህ ቤተክርስቲያን በውስጡ በርካታ ነዋየ ቅዱሳት፣ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍትና ሌሎች የገዳሙ ቅርሶች ሙሉ በሙሉ በዚህ የሽብር ቡድኑ ተዘርፈዋል።
የጮቢ ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ጨልቀባ ጨቀሳ በበኩላቸው እንደገለፁት፣ ታኅሣሥ 14 ቀን 2014 የወረዳው መቀመጫ በሆነችው ጮቢ ከተማ ሰርጎ በመግባት ቤተእምነትን ጨምሮ ትምህርት ቤት፣ አምቡላንሶች፣ ጤና ተቋማት፣ የሚሊሻ ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት አመራር ቤቶች ላይ ጥቃት በማድረስ ሙሉ በሙሉ አውድሟል።
አሁንም የሽብር ቡድኑ ነዋሪዎች ላይ ስጋት በመጫሩና በቂ የፀጥታ አካላት በአካባቢው ባለመኖራቸው ከዚህ በፊት የተፈጠረው ችግር ዳግመኛ እንዳይከሰት ስጋት አለን ማለታቸውን ኢፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

