ከ116 ግለሰቦች ላይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሞባይል ባንኪግ በማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ 80 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱ ተነገረ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት ከ116 ግለሰቦች ላይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሞባይል ባንኪግ በማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 80 ግለሰቦች ላይ ወንጀል ምርመራ በማጣራት ለፌደራል ዐቃቤ ህግ በማስተላለፍ ክስ እንዲመሰረት ማድረጉን አመልክቷል።
ተከሳሾቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከሌሎች የግል ባንኮች የሚደውሉ በማስመሰል እንዲሁም የኮምፒውተር ስርዓትን በመጠቀም አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት ወንጀሉን እንደፈጸሙ ፖሊስ ገልጿል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያብራራው፣ ተጠርጣሪዎቹ ማንነታቸውን በመሰወር፣ ሀሰተኛ ሰነዶችን እና መታወቂያዎችን በማዘጋጀት እና በመጠቀም የተበዳዮችን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በምርመራ ተረጋግጧል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስ በዋናነት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ እና የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008ን እንዲሁም የብሄራዊ የክፍያ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003ን የተላለፉ መሆናቸውን ይገልጻል።
ለወንጀል ድርጊቱ ማስፈጸሚያነት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ፦
– በርካታ የባንክ አካውንቶች፣
– የሞባይል ቀፎዎች፣
– ሲም ካርዶች እና ኮምፒውተሮች የተያዙ ሲሆን፣ ጉዳዩን ለማጣራት ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ፥ ህብረተሰቡ ከማያውቋቸውና አጠራጣሪ ከሆኑ የስልክ ጥሪዎችና መልዕክቶች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል።

