ከመጪው ከመስከረም ወር 2018 ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መንግሥት መወሰኑን የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የደመወዝ ማሻሻያውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሀገር ዐቅም የሚፈቅደውን ርምጃ እየወሰደ ነው” ብሏል።
በዚህም ለመንግሥት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መንግሥት መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በማሻሻያው ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከ4 ሺሕ 760 ብር (35 ዶላር) ወደ 6 ሺሕ ብር (44 ዶላር)እንዲያድግ እንደሚደረግም ነው የገለጸው።
እንዲሁም ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከ21 ሺሕ 492 ብር (158 ዶላር) ወደ 39 ሺሕ ብር (287 ዶላር) እንዲያድግ ይደረጋል ብሏል።
የዲግሪ ተመራቂ መነሻ ደመወዝ ከ6 ሺሕ 940 ብር ወደ 11 ሺሕ 500 ብር የሚሻሻል መሆኑን ገልጿል።
ከሲቪል ሰርቪስ ውጭ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝም ማሻሻያ እንደሚደረግበት አስታውቋል።
ይህ የደመወዝ ማስተካከያ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት መጠየቁን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ “ይሄም ለደመወዝ የሚወጣውን ጠቅላላ ዓመታዊ የመንግሥት ወጪ 56ዐ ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል” ብሏል።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት 91 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ እንዲሻሻል ማድረጉንም አስታውሷል።

