የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የፖለቲካ ግጥሞች! (ከዘመነ አፄ እስከ ኢህአዴግ)

 

“በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው፣

ደሞ እንደ መሬቱ ሳይቆራርጧቸው፡፡”

1 እንደ መግቢያ

በፈረንጆች ሚሊኒየሙ ማብቂያ ገደማ በጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኘው የአፍሪካና የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም አንድ መሳጭ የጥናት ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ የጎጃም ገበሬዎች ዘይቤያዊና ቅኔ-ለበስ ስነቃሎችን በመጠቀም ስሜትን የሚኮረኩሩና ልብን የሚነኩ መልዕክቶችን ያስተላለፉባቸው የቃል ግጥሞች ነበሩ የቀረቡት፡፡ አቅራቢው ዶ/ር ጌቴ ገላዬ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር ሲሆኑ፣ የጥናቱም ርዕስ ‹‹ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላ የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠሟቸው ፖለቲካዊ ግጥሞች›› የሚል ነበር፡፡ ከምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የተሰበሰቡት እነዚህ የቃል ግጥሞች – በተለይ ከ1983 ወዲህ በገጠሩ ማኅበረሰብ ዘንድ እየተባባሱ የመጡትን… መንግሥትን የመጠራጠር፣ የተቃውሞ፣ የምግብ እጥረትን፣ የምርት ማሽቆልቆልን፣ ድህነትን፣ ስደትንና በሠላም አብሮ የመኖር ተስፋን መጨለም በገሃድ ያሳያሉ፡፡ ያን በሀምቡርግ የቀረበ የዶክተሩን ጥናት ኋላ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም አርትዖት ሠርቶለት ለህትመት አብቅቶታል፡፡ አጥኚዎቹን አንጋፋ ምሁራንና ዋነኛ የቃል ግጥሞቹን ያመነጩትን ማኅበረሰቦች በቅድሚያ አመስግኜ፣ ለዛሬ በቻልኩት መጠን ጥናቱን አሳጥሬ ላካፍላችሁ ነው አመጣጤ። እነዚህ ከሕዝቡ መሐል የሚልቁ ስነቃሎች በሚገርም ሁኔታ አንዴ ብቻ አይደለም፣ ደጋግመው፣ የሥርዓትን ውድቀት ቀድመው የሚያመላክቱ ናቸው። ይህም በየዘመኑ ሕዝባችን ምን ያህል አስተዋይ እንደሆነና ከፍ ያለ የንቃተ-ህሊናውን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው!
በትዕግሥት ከዘለቃችኋቸው፣ እንደ እኔው እንደምትወዷቸው እርግጠኛ ሆኜ፣ በአጼው ዘመነ መንግሥት ከተነገሩ (እና በጥናቱ ከተካተቱት) ስንኞች ልጀምር፡፡ 2) የጎጃም ቃላዊ-ግጥሞች በአፄው ዘመን

በአፄው ዘመን የጭቃ ሹም፣ ነጭ ለባሽ፣ የጎበዝ አለቃ፣ ምስለኔ፣ አጥቢያ ዳኛ… እየተባሉ ይሾሙ የነበሩት በገበሬው ላይ ላደረሱበት ሰብዓዊ በደል ምስኪኑ የጎጃም ገበሬ በዘመኑ ብሶቱንና እሮሮውን በእንጉርጉሮ የገለፀባቸውን እነዚህን እናገኛለን ለአብነት፡- “በሬዬን አረደው፣ ከብቴንም ነዳው፣ ምሽቴንም ተኛት ጎጆዬን አቃጥሎ አስተኛኝ መሬት፣ ሲጨንቀኝ ሲጠበኝ ዘመድ አረግሁት፡፡”

“ታገር እኖር ብዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ ለጭቃው ዳርሁለት ምሽቴን እቴ ብዬ፡፡”

“‹‹ምሽቴን ማን ተኝቷት?›› ‹‹በሬዬን ማን አርሶት?›› አይሉም፣ አይሉም፣ ቀን የከፋ ለታ ይደረጋል ሁሉም፡፡” 3) የጎጃም ቃላዊ-ግጥሞች በደርጉ ዘመን

በደርግ ዘመን ደግሞ በሕዝቡ ላይ በኃይል ለመተግበር የተሞከሩት ጊዜ-አመጣሽ እንቅስቃሴዎች ወይም ወከባዎች ገበሬውን አስመርረውት ነበር፡፡ እነዚህ ገበሬውን ያስመረሩት ወከባዎች ምንድናቸው? ለሚል ጥቂት አብነቶችን ለመጥቀስ፣ ለምሣሌ የግብርና ልማት ፕሮጀክቶች፣ የመንደር ምሥረታና የሰፈራ ፕሮግራሞች፣ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንቅስቃሴዎች፣ የመሬት ክፍፍልና አስተዳደራዊ አፈጻጸሞች፣ የግዳጅ ኮታ ክፍያዎች፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላዎች፣ እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። የደርግ ካድሬዎች ለመንደር ምሥረታና ለሰፈራ ይፈለጋል በማለት ቤታቸውን ያፈረሱባቸው ገበሬዎች ብሶታቸውን በሚከተሉት እንጉርጉሮዎች ገልፀውት እናገኛቸዋለን፡- “መሬቴንም ውሰድ ደጄንም እረሰው፣ የምኖርበትን ቤቴን አታፍርሰው፡፡”

“ወይ አልተጣላን አልተደባደብን፣ ሰተት ብለው መጥተው ቤት አፍርሱ አሉን፡፡”

“እኽሉንም እንኩ፣ ልጃችንን እንኩ፣ የሬሳችንን መውጫ ቤታችንን አትንኩ፡፡” 4) የጎጃም ቃላዊ-ግጥሞች በኢህአዴግ ዘመን

ገበሬዎች ያንጎራጎሩለት ሶሻሊስታዊው የደርግ መንግሥት የመውደቅ ተራ ደረሰውና ወደቀ። መውደቁን ተከትሎ ለጊዜውም ቢሆን የጎጃም ገበሬ መረጋጋትና እፎይታ እንዲያገኝ ተደርጎ ስለነበር፣ መጀመሪያ ሰሞን የኢህአዴግን መንግሥት.. እና በተለይም ደግሞ የትግራይን ተጋዳዮች (ተጋዳላዮች).. በግጥም ማወዳደስ ጀምሮ ነበር ። እነዚህ በአጥኚዎቹ ከተሰበሰቡት ጥቂቶቹ ናቸው፦ “ደስ ይበልህ ጎጃም ድፍን ኢትዮጵያ፣ ያ ቀማኛ መንግሥት ገባ ምድረ ትቢያ፡፡”

“ተጥዬ ነበረ እንደ አሮጌ ቁና፣ ብድግ አርጎ አነሳኝ ኤሃዴግ መጣና፡፡”

“ትግሬ ተንቀሳቅሶ ኤሃዴግ ባይመጣ፣ ትንሽ ቀርቶን ነበር ነፍሳችን ልትወጣ፡፡”

“እኛ ምንተዳችን ያ መጣ፣ ያ መጣ? መንግሥቱ ወደቀ የማታ የማታ፡፡” አዲስ የመጣው ወያኔ-መራሹ ኢህአዴግ በበኩሉ ሥልጣን ላይ እንደወጣ (በነገራችን ላይ ገበሬዎቹ ወያኔንም ሆነ የወያኔን መንግሥት በወንድ ፆታ ሳይሆን በአንስታይ ፆታ ነበረ የሚጠሩት – ‹‹ወያኔ ከመጣች ወዲያ…›› እያሉ!) – እና ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ እንደወጣ ለጎጃም ህዝብ ብዙ ነገሮችን ቃል ገባ፣ ብዙ መልካም ብሥራቶችንም አወጀለት ለገበሬው፡፡ እነዚህ ምንድነበሩ? ለሚል ግልፅ ለማድረግ የሚከተሉትን ማንሳት እንችላለን፦ ህዝቡ ራሱ የሰላምና መረጋጋት ኮሚቴዎችን እንዲመርጥ ማድረግ፣ በደርግ ዘመን በኃይል ይተገበሩ የነበሩ የመሬት ድልድል፣ ኮታ፣ የግብርና መዋጮዎች፣ ያምራቾች የህብረት ሥራ ማኅበራት፣ ወዘተ. ሙሉ ለሙሉ እንዲፈርሱ ማድረግ፣… ገበሬዎች ቀድሞ በመንግሥት ትዕዛዝ በሰፈራ መንደር የሰሩትን ቤት አፍርሰው ያሻቸው ቦታ ሔደው ቤታቸውን እንዲቀልሱ መፍቀድ፣ የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ምልመላ እንደማይኖር ቃል መግባት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለአቅመ አዳምና ሄዋን ባይደርሱም እንደፈለጉ እንዲድሩ መፍቀድ፣ በየአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን ሌቦችና ሽፍቶች ለማጥፋት ኢህአዴግና የኮር አባላት የሚባሉት አዳዲስ ምልምል ካድሬዎች ከጎናቸው እንደሚቆሙ ማሳየት፣ እና በተለይ ደግሞ ገበሬው የጦር መሣሪያ እንደፈለገው እንደሚታጠቅና ዲሞክራሲያዊ መብቱ እንደሚረጋገጥለት ቃል መግባታቸው መጀመሪያ ላይ የሰዉን ልብ ወከክ ሳያደርገው አልቀረም!! ተጠራጣሪው የጎጃም ገበሬ ግን ቀስ በቀስ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ሁሉም ስም እየቀየረ ያው የተለመደው የደርጉ በአዋጅ-ግዛ ሲሆንበት ነገሩ.. ቀደም ሲል የጀመረውን ውዳሴ ጋብ በማድረግ… ሁኔታውን በግጥም እንዲህ በማለት ይገልጠው ጀመር፡- “እኔስ ኤሃዴግን ላመሰግነውም፣ ላማውም ቸገረኝ፣ አምኘ ብጠጋው ክላሽ ከለከለኝ፡፡”

“‹‹ዲሞክራሲ›› ብሎ አወጀ ለሕዝብ፣ ምንም ለማይጥፈው ቃል ለማያነብ፡፡”

“ኤሃዴግ ተመጣ አላረግሁም ካልሲ፣ ይዞልኝ የመጣ ባዶ ዲሞክራሲ፡፡”

እንዲህ ለውጡን በትዝብት ማየት የጀመረው የጎጃም ገበሬ ብዙም ሳይቆይ በ1983 እና በ1984 ዓ.ም. በየቀበሌው የተደረጉትን መጠነኛ የመሬት ክፍፍሎች ተመለከተ፡፡ የመሬት ክፍፍሉ ባብዛኛው ባገር ሽማግሌዎች የተከናወነ ነው ቢባልም፣ ሥልጣን ላይ የወጡትና አዳዲስ ሹመት የተሰጣቸው የኢህአዴግ ተመራጮችና የኮር አባላት፣ የኮሚቴ ሊቀመንበር፣ ሞቢላይዜሽን፣ ካድሬ፣ ምኒሻና ታጣቂ በሚባሉት አማካኝነት ነበረ በተግባር ክፍፍሉ የተደረገው፡፡ ቀስ በቀስም በመሬት ክፍፍሉ ጊዜ ልክ በደርግ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ለኢህአዴጎቹ ሹማምንቶችም ጉቦ መስጠት፣ ድግስ ማብላትና ማጠጣት፣ ወዘተ በግልፅም በድብቅም እንደ መደበኛ ተግባር መከናወን ጀመረ፡፡ በዚህን ጊዜ በጉቦ የያዘው ወይ የተዛመደው ኮሚቴ የሌለው ምስኪን ገበሬ እንዲህ በማለት ያንጎራጎር ገባ፡- “ኮሚቴም ‹‹እጅ›› አለ፣ እኔም እጅ አጠረኝ እፎካካው መሬት አምዘግዝጎ ጣለኝ፡፡”

“ለሊቀመንበሩ አንድ ባውንድ አጥቼ፣ ለኮሚቴዎቹ አንድ ጠርሙስ አጥቼ፣ ተማዞሪያው መሬት ቀረሁ ተለይቼ፡፡”

“እኔ ተኮሚቴ አበልጅ ብናሳ፣ ይሰጠኝ ነበረ ተድበሉ ማሳ፡፡”

“ተሰባት ኮሚቴ አበልጅ አጥቼ፣ አለበቆሎ እሸት ከረሙ ልጆቼ፡፡” እና በዚህ ወቅት የኢህአዴግን ዘመን አመጣሽ የፖለቲካ ጣጣ ምንተዳዬ ብሎ ቀን ከሌት ከኑሮው ጋር ግብግብ መግጠሙን የተያያዘው አብዛኛው የጎጃም ገበሬ፣ በለውጡ መጀመሪያ ኢህአዴግን እንዳላመሰገነ ሁሉ፣ ሲቆይ ግን ጠብ የሚል ነገር አጣበት፡፡ ገበሬው በለውጡ ማግስት ከልፈፋ በቀር ከቀድሞው የደርግ ዘመን የተለየ ምንም አዲስ አስተዳደራዊ አሰራርም ሆነ የኑሮ ብሥራት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ይህን እውነታ የጎጃም ገበሬ በሚታወቅበትና በለመደው የስላቅ አነጋገር – በደርግ ጊዜ በነበረ የቀድሞ ሹመኛ እንደተነገረ በማስመሰል – እንዲህ ሲል አንጎራጎረ፡- “ዋሽቼ እንዳልበላ ኢሠፓ ፈረሰ፣ አርሼ እንዳልበላ እጄ ለሰለሰ፣ ሰርቄም እንዳልኖር ኢህአዴግ ደረሰ፣ “ኧረ! ምን ይሻላል አብዬ መለሰ?”

ኢህአዴግ በህዝቡ የቃል ስንኝ እየተቋጠረበት ቀጠለ። የኢህአዴግ ሹሞች በ1989 ዓ/ም ላይ ደግሞ የመሬት ሽግሽግ ፖሊሲ እንተገብራለን ብለው ተነሱ፡፡ በምሥራቅ ጎጃም፡፡ በአማራ ክልል ብቻ በተደረገው በዚሁ የመሬት ሽግሽግ ፖሊሲ የወቅቱ የኢህአዴግ ሹመኞች ገበሬዎቹን በ3 ጎራ ከፍለዋቸው ነበር፡- 1ኛ/ ቅሪት ፊውዳል፣ 2ኛ/ ቢሮክራት፣ እና 3ኛ/ ጭቁን (ድሃ) አርሶአደር በማለት፡፡ በዚህም የገጠር ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን “ማሸጋሸግ” በሚል ስም፣ እነዚያ የኢህአዴግ ሹመኞች ማንንም ሳያማክሩ ያሰኛቸውን ቀበሌዎችና መንደሮች.. አንዱን ከአንዱ ወደ ሌላው በማጠፍ፣ መጠሪያ ስሞችን ሳይቀር እንደፈለጋቸው ለዋውጠዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን “ለመንግሥት ሳታሳውቁ የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል” ተብለው የተንገላቱ፣ የተገረፉና የታሰሩ ገበሬዎች ቁጥር በጣም ብዙ ነበር፡፡ ከመሬት ሽግሽጉ በኋላ መሬት የተወሰደባቸው የጎጃም ገበሬዎች በደላቸውንና አቤቱታቸውን ለማሰማት መንግሥት አለበት፣ ፍትህ-ርትዕ አለበት ብለው ወደሚያስቡት ወደ አዲስ አበባ በእግር ተጉዘው ነበር፡፡ የጠበቃቸው ግን እንደደረሱ በፖሊስ ተከበው የመረምረም ፅዋ ነበር። ከዱላም አልፎ ተርበውና ተጠምተው ለሳምንታት ከተንገላቱ በኋላ “የመሬት ሽግሽጉን ያፀደቀው እዚያው የክልላችሁ የአማራ መንግሥት ስለሆነ ባህርዳር ሄዳችሁ ጠይቁ!” የሚል ቀጭን መልስ ተሰጥቷቸው.. ሲመለሱ የታሰሩም፣ የአዲሳባው ዱላ ሳይበቃቸው ዳግመኛ የተደበደቡም ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይ በገበሬው ዘንድ ለችግሮቻቸው በዋነኝነት ዝነኛ ሆኖ ብቅ ያለው ስም የኢህአዴግ ‹‹የኮር አባል›› የሚለው ሆነ። የኮር አባሎች ናቸው ተብሎ የገበሬው መሬት እየተቀማ በስማቸው የተላለፈላቸው ነበሩ፡፡ መሣሪያ ታጥቀው የሥርዓቱ ጆሮ-ጠቢና በኃይል አስጠባቂ ሆነው የተገኙም ነበሩ፡፡ በመሆኑም የጎጃም ገበሬ ቁጣ በእነዚሁ ገበሬው በጅምላ “የኮር አባል” ብሎ በጠራቸው የኢህአዴግ አስፈጻሚ ሹመኞች ላይ ነደደ። የሚከተሉት ግጥሞች ያንን የህዝቡን ስሜት የሚያንፀባርቁ ናቸው፦ “አሥራት ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ፣ ኮታ ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ፣ የኮር አባል መጣ የባሰው ቀማኛ፣ መሬቴን ወሰደው ሰፍሮ በመጫኛ፡፡”

“ጣሊያን አልመጣብን ተኩስ አልተተኮሰ፣

ወይ ወራሪ አልመጣ ችግር አልደረሰ?

በኮር የተነሳ አገሩ ፈረሰ፡፡”

“ወትሮም ነገረኛ ነበረ ተጥንት፣

ኮር ነው ያስቸገረን ጠማማው እንጨት፡፡”

እኔስ አርስ ነበር የገበሬው ልጅ፣

እኔስ አርስ ነበር የገባሩ ልጅ፣

መሬቴን ቢለኩት ቢወስዱት ነው እንጅ፡፡”

ቀጥሎ የቀረበው አንድ ግጥም ደግሞ.. መሬታቸው በኢህአዴግ ካድሬዎች በግድ የተወሰደባቸው የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የደረሰባቸውን አሳዛኝ ግፍና ኢሰብአዊ በደል.. ባጠቃላይ ለጎጃም ሕዝብ፣ ለወገኖቻቸው ጩኸታቸውንና ኀዘናቸውን አቤት ሲሉ የሚሰሙበት ግጥም ነው፡- “ይታይህ ማቻክል ይሰማህ ጎዛምን፣ ይታይህ በረንታ ይሰማህ ጥላትግን፣ እግዞ በል እነሴ ጎንቻና ሣር ምድር፣ እግዞ በል አዋበል እግዞ በል አነደድ፣ እንዴት ይወሰዳል መሬታችን በግድ?”

“ወይ አገሬ ኧረ! አገሬ ጎጃም ወሰዱት መሬቴን እርስትና ጉልቴን፣ የራብ መከለያ ልብስና ቀለቤን፣ ወሰዱት መሬቴን ሰፍረው በገመድ፣ ተእንግዲህ ደካማው፣ ተእንግዲህ አሮጉ ኧረ! ወዴት ልግባ? ኧረ የት ልሂድ?” እንዲህ እንዲህ እያለ የጎጃም ገበሬ የገጠመው ብዙ ነው፡፡ ያንጎራጎረው መዓት ነው፡፡ ጥቂቱን ብቻ ነው መርጦ ማቅረብ የሚቻለው፡፡

እንዲሁ ደግሞ በኢህአዴግ (‹‹በዘመነ ወያኔ››) መሬታቸው የተወሰደባቸው የጎጃም ገበሬዎች.. የሞት ያህል ያስጨነቃቸውን የረሃብ አደጋ፣ የመኖር ህልውናቸው ያከተመ በመሆኑ የተሰማቸውን ውስጣዊ ስሜት፣ ብሶታቸውን… “ልጆቼን ምን ላብላቸው?” “በምን ላሳድጋቸው?” እያሉ በእንግርጉሮዎቻቸው ያሰማሉ፡- “አልሞተ መስሎታል እሬሳው ታልወጣ፣ ያባቱን ባድማ ሲካፈሉት በእጣ፡፡”

“ተዘንድሮው እራብ የከርሞው ይብሳል፣

መሬቱ ተወስዶ ምኑ ይታረሳል?”

“ዘመነ ወያኔ! ዘመነ ኢህአዴግ!

መሬቴ ተወስዶ ልጅ በምን ላሳድግ?”

“በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው፣

ደሞ እንደ መሬቱ ሳይቆራርጧቸው፡፡”

እላይ በተገለጹት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የጎጃም ገበሬዎች ከኢህአዴግ አባላት፣ የግብርና ባለሞያዎችና ኮሚቴዎች ጋር ከፍ ያለ ቅሬታ ውስጥ ገብተዋል። ግን አፍ አውጥተው ለመናገርና ተቃውሟቸውን ፊትለፊት ለማሰማት የሚሞክሩት፣ ከዚያው መሐል በወጡና በጥቅም በተያዙ የኢህአዴግ ታጣቂዎችና የኮር አባላት እየታደኑ ይታሰሩ ነበር።፡ ታዲያ እነዚያ የጎጃም ገበሬዎች በተወለዱበት መንደራቸው፣ ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር በሰላም አብረው መኖር ባለመቻላቸው ሥርዓቱ ያመጣባቸውን የእርስ በእርስ ግጭትና አዳኝ-ታዳኝነት በምሬት አስተውለው… ብሶታቸውንና ሮሮዋቸውን እንደሚከተለው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡- “ምን ዓይነት ጣጣ ነው? ምን ዓይነት መከራ? ሰው እንዴት አይኖርም ታብሮ አደጉ ጋራ?”

“የኛ ዳኞቻችን መሬታችን ናቸው፣

በሮቻችን ናቸው፣

አላስቀምጥ ያሉን ኮሚቴዎች ናቸው፡፡”

“ጥረት ባደረጉ እጅ ላለመስጠት፣

ጥረት ባደረጉ ብረት ላለመስጠት፣

ቃላቸው ተቀድቶ ገቡ ተውህኒ ቤት፡፡”

“ገበሬን አትንኩት! እዚያው ይቀመጥ፣

ጭቁኑን አትንኩት! እዚያው ይቀመጥ፣

ብዙ ጉድ ይወጣል ሲገለባበጥ፡፡”

“እሄዳለሁ እንጅ ምነ አለመሄዴ?

የኮሚቴን ደባ እያወቀው ሆዴ፡፡”

“የኮሚቴን ደባ ተማይ ተቀምጨ፣

የወያኔን ደባ ተማይ ተቀምጨ፣

የካድሬውን ደባ ተማይ ተቀምጨ፣

ስደት መሄዴ ነው አገር አቋርጨ፡፡”

“ዓባይ ገመገሙ ታየኝ እዚያ ማዶ፣

የሚሻገርበት ወንድ ልጅ ተናዶ፣

መሬቱ ተወስዶ ቤቱ ሁኖ ባዶ፡፡”

“ሞፈሩን ቀንበሩን ክተቱት በጎታ፣

እናርስበታለን ቀን የወጣ ለታ፡፡”

እነዚህ ገበሬዎች አንዳንዴ ሲያንጎራጉሩ የሚገኙት ግጥም ከመንደራቸውና ካካባቢያቸው አልፎ ስለ ሀገር ፖለቲካ የሚያጠነጥንበት ጊዜም አለ፡፡ ከደርግ ሶሻሊስታዊ መንግሥት ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያን በዘርና በጎሳ የከፋፈለውና በገጠሩ የጎጃም ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ዘር ላይ ያተኮረው ፖለቲካዊ ተፅዕኖ በአማራው ሕዝብ ላይ በአጠቃላይ እየደረሰ ያለውንም በደል በማንሳት… “የግፉ ሥርዓት ምሰሶና ተጠያቂ ናቸው” የሚሏቸው እነማን እንደሆኑም በቃልግጥሞች እስከ መግለፅም ደርሰው እናገኛቸዋለን የጎጃምን ገበሬዎችን፡- “ሲከፋፋን ጊዜ ብናንጎራጉር፣ ‹‹እነዚያ ነፍጠኞች›› እንባል ጀመር፡፡”

“ወይ አገሬ ጎጃም አጋሙ ግራሩ፣

ሁሉንም ቆረጡት ለማገር እያሉ፡፡”

አማራን ‹‹ተኛ›› አለ ትግሬውን ‹‹ነግድ››፣

እንዲህ ነው ያገር ልጅ ስንፈቃቀድ?”

“እኛ መች ፈለግነው የትግራዩን ጠጅ፣

እኛ መች ፈለግነው የስሜኑን ጠጅ፣

እየበጠበጡ ያፋጁናል እንጅ፡፡”

በአጠቃላይ እነዚህ በምሁራን ጥናት ከምሥራቅ ጎጃም የተሰባሰቡት የጎጃም ገበሬዎች የቃል ግጥሞች አስገራሚ ናቸው፡፡ ስነቃሎቹ በአንድ ሰው የህይወት ዘመን – ከአፄው ዘመን እስከ ደርግ ዘመን፣ ከደርግ እስከ ወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን፣ እና ስለመጪውም ሁኔታ – ማኅበረሰቡ የተሰማውን ስሜትና ያሳለፈውን እውተኛ ኑሮ፣ ህይወት፣ የደስታና የሀዘን፣ የመከራና የቁጭት ስሜት ግልጥልጥ አድርገው ያሳያሉ፡፡ ስለ ማኅበረሰብ ስናጠና ከነወጉና ልማዱ፣ ከነ ስነቃሉ፣ ከነ ቃላዊ ግጥሞቹ፣ ከነ እንጉርጉሮዎቹ ካላጠናነው ምሉዕ ምስል እንደማናገኝ እነዚህ የማኅበረሰባችንን አስገራሚ አስተውሎት የሚያሳዩ አስገራሚ ቃላዊ ግጥሞች ምስክሮች ናቸው፡፡ አንድ ቀን የሀገራችን ገበሬዎች ቀን ወጥቶላቸው.. ቃላዊ ቅርሶቻቸው በሚገባ ተጠንተው… ማንነታችንንና ያሳለፍናቸውን ዘመናት በሚገባ እንድናውቅ ዕድሉን እደምናገኝ አምናለሁ። በቅርብ ዓመታት በሀገራችን የተደረጉ የሚታዩ ጥረቶችም ይህን እሞነት የሚያጠናክሩ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ‹‹ፎክሎር›› (የማኅበረሰብ ስነቃሎች)) የጥናት መስክ በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ መከፈቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ለወደፊቱ ብዙ ፍሬዎችን እንጠብቃለን፡፡ (በቅርቡ በትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥ የተነገረው የግዕዝ ቋንቋም የማኅበረሰባችንን ከዘመን የተቀሰመ ጥበብ ለትውልድ በማስተላለፍ የሚኖረውን ሚና መገመት የሚከብድ አይመስለኝም!) ለአሁኑ በዚህ የጎጃም ገበሬዎችን ማኅበረሰባዊ ቃለግጥሞች በማጥናት፣ በዓለማቀፍም መድረክ በማቅረብ፣ ዕውቀትን በመሰነድ.. የተሳተፉትን ሁሉንም ምሁራን.. ከልብ በመነጨ አክብሮት አመሰግኜ አበቃሁ፡፡ እስከዚህ ዘልቃችሁ ያነበባችሁትን ወዳጆችም፣ እናንተን አለማድነቅና አለማመስገን እንዴት ይቻላል? ተባረኩ! ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን አብዝቶ ይባርክ! ሰናይ ጊዜ! (Asefa hailu)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe