ፕሬዝዳንት ፑቱን የትኛውንም የሰላም ስምምነት ከዘለንስኪ ጋር አይፈርሙም ምክንያቱም ዘለንስኪ በእኛ ዘንድ አሁን ህጋዊ ፕሬዝዳንት እንዳልሆነ ነው የምናውቀው ሲሉ ከፍተኛ ዲፕሎማቶቹ ተናግረዋል፡፡ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌላቭሮቭ ፑቲን ምንም አይነት ስምምነት ከዘለንስኪ ጋር የሚያደርጉበት አግባብ አይኖርም ብለዋል፡፡
ከአላስካው ንግግር በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁለቱንም መሪዎች ፊት ለፊት ለማገናኘት እቅድ እንዳላቸው በገለጹበት ወቅት ሩሲያ መሪዎቹን ሊያገናኝ የሚችለው አጀንዳ አልተዘጋጀም እናም ይህ እስካልሆነ ድረስ አይገናኙም ነበር ያለችው፡፡ ሰርጌላቭሮቭ እሁድ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ግን ዘለንስኪ አሁን ያልተመረጡ ፕሬዝዳንት ናቸው እናም ህጋዊ ካልሆነ ሰው ጋር ምንም አይነት ስምምነት መፈራረም አይቻልም ብለዋል፡፡
ላቭሮቭ ሩሲያ ዘለንስኪ የዩክሬን ፕሬዝዳናት ናቸው ብላ እውቅና እንደማትሰጥም በይፋ ተናግረዋል፡፡
አክለውም እኛ ዘለንስኪን የምንመለከተው ያለ ህጋዊ መንገድ በስልጣን ላይ እንዳለ አደርገን ነው፤በዚህ ስልጣኑ ልናገኘው እንችላለን ነገር ግን ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባው ህጋዊ ዶክመንቶችን ለመፈራረም ዘለንስኪ ብቁ አለመሆኑን ነው ብለዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ እያቀረበች ነው የምትገኘው፡፡ በርግጥ ዩክሬን ባለፈው ዓመት የካቲት ነበር ምርጫ የምታደርገው ነገር ግን በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ምርጫውን ማድረግ አልቻለችም፡፡
ሩሲያ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ነው የዘለንስኪ ስልጣን አብቅቷል የሚል ክስ የምታቀርበው፡፡ ሩሲያ ይህን ጫና የምታሳድረው ለዩክሬን ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት ድጋፋቸውን እንዲተውት ለማድረግና ዘለንስኪም ያለ ምርጫ ነው በስልጣን ላይ ያለው የሚለውን ለመግለጽ በሚል ነው ተብሎ ይነሳል፡፡
ነገር ግን አሁንም ድረስ የምዕራብ አገራት ዘለንስኪ የዩክሬን ፕሬዝዳንት መሆናቸውን አምነው የሚቀበሉ ናቸው፡፡ የዩክሬን ህገ መንግስት ምርጫን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እስከሚመጣ ድረስ በስልጣን ያሉት ፕሬዝዳንት ህጋዊ ሆነው እንደሚቀጥሉ ይደነግጋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ውስጥ ሆኗ የነጻነት በዓሏን አክብራለች፡፡ ዩክሬን የዘንድሮውን ጨምሮ ለአራት ተከታታይ ጊዚያት ሩሲያ በከፈተችባት ጦርነት ውስጥ ሆና አክብራለች፡፡ ከሶቪት ህብረት ከተገነጠለችና ራሷን ከቻለች ዘንድሮ 34ኛ ዓመቷን ደፍናለች፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የነጻነት በዓላቸውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው፤ሰላማችንም መወሰን ያለበት በእኛው ነው፤ዓለምም ይህን ሊያውቀውና ሊያከብረው ይገባል ብለዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል የሰላም ንግግሮች እንኳን የሚቀጥሉ ቢሆንም፤ሩሲያ ከዘለንስኪ ጋር የመገናኘት ፍላጎቷ እጅግ ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሞስኮ ዘለንስኪን የዩክሬን ፕሬዝዳንት መሆናቸውን አምና የምትቀበል አይደለችም፡፡
የዩክሬን የፓርላማ አባል የሆኑ ሴትም ለጀርመን ድምጽ በሰጡት ኢንተርቪው ሩሲያ ዩክሬንን ለማጥፋት ከተነሳች ከሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ አልፏታል፤ነገር ግን እኛ ዩክሬናዊያን አሁንም በአንድነት በመቆም እየተዋጋን ነው ብለዋል፡፡ በርግጥ በእነዚህ ጊዚያት ብቻችን አይደለንም በርካታ ወዳጆቻችንም ከእኛው ጋር ቆመዋል በማለት ገልጸዋል፡፡
አክለውም ይህ አሁን የተጀመረው ጦርነት ለቀጣይ ትውልድ መተላለፍ እንደሌለበት ስለምናምን ነው እየተዋደቅንና የትኛውንም መስዋዕትነት እየከፈልን የምንገኘው ብለዋል፡፡
ሩሲያ ከአላስካው ንግግር በኋላ በአንዳንድ ፍላጎቶቿ ዙሪያ ለሰላም ሲባል መለሳለስ ማሳየቷን ሰርጌላቭሮቭ ገልጸው፤በአንጻሩ ዩክሬን ይህን ለማድረግ አልፈቀደችም በማለት ተናግረዋል፡፡ ሩሲያ መለሳለስ አሳይታባቸዋለች ከተባሉት ነጦቦች መካከል የደህንነት ዋስትና ለዩክሬን መሰጠት አለበት በሚለው ጉዳይ ለመነጋገር መፍቀዷ አንዱ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
ለሞስኮ ዩክሬን የደህንነት ዋስትና እንድታገኝ በሚለው ላይ ለመወያየት መፍቀዷ ምንም የሚያሳጣት ነገር እንደማይኖር ይነገራል፡፡
ለኬቭ ግን የደህንነት ዋስትና ከኔቶ አባልነት ውጪ ማለት ትርጉም የሌለው እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡
ከአላስካው ንግግር በኋላ 10 ቀናቶች አልፈዋል፡፡ ዘለንስኪ አሁንም ጠላቶቻችንን እየተዋጋን ነው እያሉ ሲሆን፤ሩሲያ ደግሞ ስለ ሰላም እየሰራሁ ነው ብትልም ዘለንስኪን ግን እንደ ፕሬዝዳንት እየተመለከተቻቸው አይደለም፡፡//

