የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ሶማሊያ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ለማድረግ ዝግጁ ነች አሉ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ሶማሊያ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ለማድረግ ዝግጁ ነች አሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ እስራኤል ጦሯን ወደ ሶማሌላንድ የምታስገባ ከሆነ ጦርነቱ የማይቀር ነው ብለዋል፡፡

የእስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠት ለቀጠናው ስጋት ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ተናገሩ፡፡

እስራኤል ይህንን ውሳኔ ያሳለፈችው ለራሷ ጥቅም ቢሆንም ይዞት የሚመጣው ችግር ግን የሶማሊያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ህዝብ የሚጎዳ መሆኑን መናገር ይቻላል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ እስራኤል ከሶማሊ ላንድ ጋር በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ተስማምታለች ብለዋል፡፡ አንድኛው በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማዊያንን ያለ እኛ ሶማሊዎች እውቅና በምድራችን ለማስፈር፡የጦር ቤዝ መገንባት እና ሶማሊላንድ ደግሞ የአብርሃም አኮርድ ስምምነትን ለመቀበል ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ እንዲህ አይነቱን ክስ ያሰሙ እንጂ እስራኤል ፍልስጤማዊያንን ወደ ሶማሊያ የማምጣት እቅድ እንዳላት ያለችው ነገር የለም፡፡

የእኛ ጥያቄ ለምን እስራኤል በሶማሊያ የጦር ቤዝ እንዲኖራት ፈለገች የሚለው ነው የጦር መሠረት ማለት የቱሪስት ስፍራ ማለት አይደለም፤የጦር ቤዝ ማለት ለመከላከል ወይም ለመጥቃት የሚውል ነው ብለዋል፡፡

እስራኤል ደግሞ በሶማሊያ ይህን ለማድረግ የሚያስችላት ቦታ የላትም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ላለፉት 30 ዓመታት ያህል ራስ ገዝ ሆና የዘለቀችውን ሶማሊላንድን በንግግራቸው የሶማሊያ አንድ አካል አድርገው ነበር ከአል ጀዚራ ጋር ቃለ ምልልሱን ሲያደርጉ የቆዩት፡፡

እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና እንድትሰጥ ያደረጋት ምክንያት የደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የእስራኤል ወደ ቀይ ባህር መጠጋት በየመን እና በቀይ ባህር ጠላቷ ሆኖ የዘለቀውን የሁቲ አማጺ ሃይልን ለመከላከል እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህ የእስራኤል አመክንዮ ግን ለእነ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክዋ ሶማሊያ ተቀባይነት የለውም፤ይልቁንስ ሉዓላዊ መብታችን ተጥሷል የሚል ክስ ነው ሲቀርብ የሚሰማው፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የቱርክ ወደ ሶማሊያ መምጣት ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት አይደለም ብለዋል፡፡ ቱርክ በዚህ ስዓት ሶማሊያ ከጠላቶቿ እራሷን እንድትከላከል የማድረግ ድጋፍ ነው እያደረገች ያለችው ብለዋል፡፡

እስካሁን እስራኤል ጦሯን ወደ ሶማሊያ አላስገባችም ያስገባች ቀን ግን ባለን አቅም ሁሉ እንዋጋታለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

እስራኤል ለሶማሊያ እንደ ሀገር የመቀጠል ስጋት የምትሆን ከሆነ በምናደርገው የመላከል ውጊያ ከእኛ ጋር አብረውን የሚሰለፉ የተወሰኑ ሀገራት ጭምር ይኖራሉ ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ከእስራኤል በተጨማሪ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስን የተመለከተ ጉዳይም በቆይታቸው አንስተዋል፡፡ በቀደመው ጊዜ አቡዳቢ የሞቃዲሾ የቅርብ አጋር ነበረች፤አሁን ግን ችግር በመካከላችን ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የግንኙነቱን መሻከር የፈጠረውም ዩኤኢ ሶማሊያን እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገር ከመቁጠር ይልቅ እዚህም፤እዚያም ላሉ ተገንጣዮች የሀገርነት እውቅና በመስጠት ስምምነቶችን ማድረግ ትፈልጋለች ይህ ነው ትልቁን ክፍተት የፈጠረው ብለዋል፡፡

ብዙ ጊዚያትንም ታግሰን ቆይተን ነበር አሁን ግን ለሶማሊያ የግዛት አንድነት አደጋው የከፋ ሆኖ ሲመጣ የነበረንን የጋራ ትብብር በሙሉ እንድናቋርጥ አስገድዶናል ብለዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ግን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን አልተቋረጠም ኢምባሲያችን በአቡዳቢ አለ፤የእነርሱም በሞቃዲሾ አለ ትብብሮች ናቸው የተቋረጡት በማለት ተናግረዋል፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe