የቀድሞ የቴዲ አፍሮ ማናጀር አዲስ ገሰስ ከዚህ ዓለም ተለየ

ታዋቂው የሙዚቃ አዘጋጅ (Promoter) እና በማኔጅመንት ስራው በርካታ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያንን ለዓለም መድረክ ያበቃው አቶ አዲስ ገሰሰ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
በተለይም እንደነ አስቴር አወቀ፣ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና ሌሎች በርካታ ታዋቂ ከዋክብትን በዓለም አቀፍ መድረክ በማስተዋወቅ ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል።
አዲስ ገሰሰ የቦብ ማርሌይ ልጅ የዚጊ ማርሌይ ማናጀር የነበረ ሲሆን ዚጊን እንደ አጎትም ሆኖ አሳድጓል። የታላቋ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) ማናጀርም ሆኖ ብዙ ሰርቷል። የዘመናችን የሙዚቃ ንጉስ የአሰላሳዩ የቴዎድሮስ ካሳሁን( ቴዲ አፍሮ) ማናጀርም ነበር ፤ከጌታቸው ማንጉዳይ በፊት። በአሜሪካ ወንድሞቹ ይሰሩበት የነበረውን ዋይልድ ሔር የሙዚቃ ክለብ አብሮ በመግዛት የግል ንብረት አድርገው ሲሰሩ በደንብ ያግዛቸው የነበረ የቤተሰቡ መከታና ታላቅ ወንድም ነበር።
ወደኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ እንደነ ሔዋን፣ ድበኩሉ፣ ሐሌሉያ፣ ኃይሉ አመርጋና ሌሎችንም ያቀፈውን “ጃኖ ባንድ” ን የመሰረተውና ለዝና ያበቃው አዲስ ገሰሰ ነው ።
አዲስ ገሰሰ እጅግ ትሁት የተረጋጋና ምክር ወይም ድጋፍ ለመጠየቅ ወደሱ የሚሔድን ሰው (ትልቅም ይሁን ትንሽ) ጆሮ ሰጥቶ በማዳመጥ የሚችለውን የሚደግፍ ሰው ነበር።

አቶ አዲስ ገሰሰ በሙዚቃው ኢንደስትሪ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያሳረፈ፣ የብዙዎችን ህይወት የቀየረ እና የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ያቆመ ታላቅ ሰው ነበረ። ይህ የሙዚቃ ማኔጅመንት ባለሙያ፣ ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፉትን የሬጌው ንጉስ የቦብ ማርሊ ቤተሰቦችን ጨምሮ የበርካታ ታዋቂ ሙዚቀኞች የጀርባ አጥንት በመሆን አገልግላል። የእሱ የህይወት ጉዞ ከኢትዮጵያ ጀምሮ፣ በቺካጎ፣ ጃማይካ፣ ኒው ዮርክ እና በመጨረሻም ኒው ጀርሲን ያዳረሰ ረዥም እና አስደናቂ መንገድ ነበር።
አቶ አዲስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ፣ ከ30 ዓመታት በፊት ወደ አሜሪካ አቅንቶ ማኔጅመንት አጠና። ከዚያም  ህይወቱን ሙሉ ለሙሉ ለወንድሞቹ የሙዚቃ ስኬት አዋለ። ወንድሞቹና ጓደኞቻቸው የመሰረቱት “ዳሎል” የተሰኘው ባንድ፣ ከኢትዮጵያዊ ሙዚቃ ወደ ሬጌ በማዘንበል፣ በአቶ አዲስ አመራር ስር በቺካጎ ስሙን ማግነን ጀመረ።
በ1982 የቦብ ማርሊ ባለቤት ሪታ ማርሊ ባቀረበችላቸው ጥሪ መሰረት፣ ዳሎል ባንድ በጃማይካ ኪንግስተን በተካሄደው የመጀመሪያው የቦብ ማርሊ መታሰቢያ ላይ ለመጫወት በቅቷል። አቶ አዲስ ሪታ ማርሊ በባለቤቷ ሞት እያዘነች በነበረችበት ወቅት የሰጧት ድጋፍ፣ ጠንካራ ወዳጅነትን ፈጠረ። ይህ ግንኙነት ዳሎል ባንድ ከ1988 እስከ 1991 ድረስ የዚጊ ማርሊ ይፋዊ ባንድ እንዲሆን አስችሎታል። ዳሎል ባንድ በ “Conscious Party” አልበም ፕላቲነም፣ እና በ “One Bright Day” አልበም ጎልድ ደረጃ በመድረስ፣ ይህን ታሪካዊ ስኬት ያገኘ የመጀመሪያው የኢትዮጵያውያን ባንድ ለመሆን በቅቷል።
አቶ አዲስ ከሪታ ማርሊ ጋር በመሆን የቦብ ማርሊን ‘Legend’ አልበም ዓለም አቀፍ ጉብኝት አደራጅተዋል። ከሁሉም በላይ ግን፣ አቶ አዲስ በ2005 በአዲስ አበባ የተካሄደውንና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ የታደመበትን ታሪካዊውን “Africa Unite” ኮንሰርት በዋናነት የጠነሰሰው እሱ ነበር። ይህ ኮንሰርት የቦብ ማርሊን 60ኛ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ፣ የቦብ ማርሊ ቤተሰብ፣ አንጀሊክ ኪጆን ጨምሮ በርካታ ከዋክብትን በአዲስ አበባ ያሰባሰበና ስለ ኢትዮጵያ አዎንታዊ ገጽታ ለዓለም ያሳየ ታላቅ ኩነት ነበር።
አቶ አዲስ የዓለም አቀፍ ከዋክብትን ከማስተዳደር ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ዓለም መድረክ ለማሸጋገር ትልቅ ህልም ነበረው። ለዚህም ነው “አዲስ ማኔጅመንት” የተሰኘውን ድርጅቱን መስርቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን የደገፈው።
ታዋቂውን ድምጻዊ ቴዲ አፍሮን በማግኘትና ለረጅም ጊዜ ማኔጀሩ በመሆን አገልግላል። እንዲሁም፣ ታዋቂዋን ድምጻዊት ጂጂን በአጋጣሚ ቤቱ ውስጥ ካገኛት በኋላ፣ ችሎታዋን አይቶ፣ ኒው ዮርክ እንድትመጣ በመምከር፣ ከታዋቂው የአይላንድ ሪከርድስ መስራች ክሪስ ብላክዌል ጋር አስተዋውቀዋት፣ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ውል እንድትፈራረም አድርገዋል።
አቶ አዲስ ዓለም አቀፍ ኔትዎርክ ያላቸውና ስኬታማ ሲሆን፣ እንደቅርብ ወዳጆቻቸው ምስክርነት እጅግ ትሁት ሰው ነበር። ኒው ጀርሲ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሹራብና አጭር ሱሪ ለብሶ ከሶስት ዓመት ልጁ ሀና ጋር ጊዜ ማሳለፍን የሚወድ አባት ነበር። ከሙዚቃ ስራው በተጨማሪ በቺካጎ የሬጌ ክለብ፣ በኢትዮጵያ የእርሻ ስራ እና በ “One Love Africa Foundation” አማካኝነት በኢትዮጵያ ገጠራማ ክፍሎች ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ሰፊ ራዕይ ነበረው።
አቶ አዲስ ገሰሰ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ በክብር ያስጠራ፣ የሙዚቃውን ኢንደስትሪ ያሳደገ እና ለብዙዎች መነሻ የሆኑ ታላቅ ሰው ነው። በድንገተኛ ህልፈቱ የሙዚቃው ዓለም፣ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቻቸው፣ እንዲሁም አድናቂዎቻቸው ጥልቅ ሀዘን ላይ ይገኛሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe