“በኬንያ የዩኒቨርስቲ ሌክቸረር በወር 1,200 ዶላር ሲከፈለው በኢትዮጵያ በወር በአማካይ 89 ዶላር ያገኛል’
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሆነውን የግብር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጥምርታን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት፣ የሀገሪቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ምጣኔን ከ15% ወደ 17.5% እንዲያድግ ምክረ ሃሳብ መቅረቡን ካፒታል ጋዜጣ ዘገበ።
ይህንን የግብር ምጣኔ ማሳደግ፣ የሀገሪቱን የግብር ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሳድግ እንደሚችል ተነግሯል።
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፊስካል ጥናት ተቋም (IFS) በጋራ ባዘጋጁት አዲስ ጥናት፣ የኢትዮጵያ የ15% የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ከብዙ የምስራቅ አፍሪካ እና የደቡብ ሰሃራ አፍሪካ ሀገራት ምጣኔዎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።
ለምሳሌ፣ የኬንያ የ ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ምጣኔ 16% ሲሆን፣ የሩዋንዳና የዩጋንዳ ደግሞ 18% ነው። የደቡብ ሰሃራ አፍሪካ ሀገራት አማካይ ምጣኔም 17.5% መሆኑን አመልክቷል።
ጥናቱ አክሎም፣ የ ተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔን ወደ 17.5% ማሳደግ ብቻ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በተጨማሪ 0.4% ነጥቦችን ከ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቁሟል።
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከዚህ በፊት ታክስ አልተሰበሰበባቸው የነበሩ እንደ ነዳጅ ያሉ ምርቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ መጀመሩ ትልቅ አዎንታዊ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
“የኢትዮጵያ ታክስ-ለ-ጂ.ዲ.ፒ ምጣኔ፡ የማነፃፀሪያ ግምት እና የአፈጻጸም ትንተና” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ ጥናት፣ የኢትዮጵያ የታክስ-ለ-ጂ.ዲ.ፒ ምጣኔ በ2022/23 በጀት ዓመት ወደ 7.5% ዝቅ ማለቱን ያሳያል።
ይህ ቁጥር በ2014/15 ከነበረው ከፍተኛው 12.4% ጋር ሲነፃፀር 4.9 በመቶ ነጥብ ቅናሽ አሳይቷል። ለዚህ ከፍተኛ የገቢ ቅናሽ ዋና ዋና ምክንያቶችም ዉስጥ መዋቅራዊ ለውጦች ፣የፖሊሲ ልዩነቶች እና ዝቅተኛ የታክስ ተገዢነት መሆናቸውን በዝርዝር አስቀምጧል።
ሆኖም መንግስት የዚህ አይነት ጥናት ሲያደርግ የዜጎችን ገቢ ክግምት ማስገባት አለበት የሚሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ለምን ለመንግስት የሚጠቅመውን ብቻ እየመረጠ ልምድ እንደሚወስድ ግልዕ አይደለም ይላሉ። እነዚህ የመንግስት ሰዎች መረጃውን እነሱ ብቻ የሚያውቁት፣ ህዝቡ ግን ደደብና ያሉትን ብቻ የሚያውቅ ይመስላቸዋል የሚሉ አንደ የኢኮኖሚ ባለሙያ < ለምሳሌ በተተጠቀሱት አገራት ማለትም ኬኒያ 16%፣ ዩጋንዳና ርዋንዳ 18% VAT ይሰበስባሉ ይላል። ከኢትዮጵያ በቀደም ተከተል አንድ በመቶና ሁለት በመቶ ነው ብልጫቸው።
ነገር ግን በእነዚሁ አገራት ለምሳሌ አንድ በህዝብ (public) ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ሌክቸረር በወር የሚያገኘው ደመወዝ ከኢትዮጵያ በእጅጉ ይልቃል። በኬንያ የዩኒቨርስቲ ሌክቸረር በወር 1,200 ዶላር፣ በዩጋንዳ 1,800 ዶላር እና በርዋንዳ ደግሞ 535 ዶላር በወር አማካይ ደመወዝ ይከፈላቸዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ በተመሳሳይ የአካዳሚክ ማዕረግ ያለ የዩኒቨርስቲ ሌክቸረር በወር በአማካይ 89 ዶላር ያገኛል። ልዩነቱን ማንም ሰው የማረዳው ነው።
ስለዚህ ከዚህ አንፃር ሲታይ በኬንያ፣ ዩጋንዳና ርዋንዳ ያሉ ስራተኞች ደመወዛቸው የተሻለ የመግዛት አቅም (purchasing power) ስለሚፈጥራላቸው 16 እና 18 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ከሚሸምቱት ሸቀጥና አገልግሎት ቢከፍሉ አቅሙ አላቸው።
በአንፃሩ የኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ላይ ደግሞ ጭራሽ ግብር ምጣኔ ይቀነስ፣ ደመወዝ ይጨመር፣ ቫት ይቅር እየተባለ ቢጠየቅም መንግስት የግብር ጭማርውን ልምድ ሲጠቅስ ለምን የእነዚህን አገራት ሰራተኛ ደመወዝ እና የመግዛት አቅም ስለማሳደግስ አብረው ልምድ አይወስዱም? > ሲሉ ይጠይቃሉ?

