የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ 10 ቢሊዮን ዶላር የወጣበትን ትልቁን የኤሌትሪክ ማመንጫ ለማፈንዳት ዛቱ

” የጊዜ ገደቡን ያራዘሙት የኢራን አጸፋዊ እርምጃ ስላስፈራቸው እንጂ በድርድር አይደለም ” – የኢራን ዜና ወኪሎች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም አስቀምጠውት የነበረውን የ48 ሰዓታት የጊዜ ገደብ ወደ አምስት ቀናት ማራዘማቸውን አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የጊዜ ገደብ ያራዘሙት ከቴህራን ጋር በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ግጭት ” በጣም ጥሩ እና ውጤታማ ” ውይይቶችን ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ ገልጸዋል።

ውይይቱ ዋነኛው አጀንዳ ስለ ኢራን የኒውኩሌር ፕሮግራም እንደሆነ አመልክተዋል።

” ለሰላም ሲባል የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመተው ልትስማማ ትችላለች ” ብለዋል።

” ነገ ጠዋት፤ በእነርሱ የሆነ ሰዓት ላይ፣ ለመገንባት 10 ቢሊዮን ዶላር የወጣበትን ትልቁን የኤሌትሪክ ማመንጫ ፋብሪካቸውን ለማፈንዳት እየጠበቅን ነበር ” ሲሉ ተናግረዋል።

” በጣም ጥሩ ነበር፤ የገንዘብ እጥረት አልነበረም፤ በአንድ ተኩስ ይወድማል፤ ይፈራርሳል። ለምን ይህን ይፈልጋሉ ? እነርሱ ናቸው የደወሉት፤ እኔ አልደወልኩም። እነርሱ ደወሉ። ስምምነት ላይ መድረስ ፈልገዋል ” ብለዋል።

” እኛ ከስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ፈቃደኞች ነን። ጥሩ ስምምነት መኖር አለበት፤ እና ሌላ ጦርነት ሊኖር አይችልም፤ የኒውለክሌር ጦር መሣሪያ አይኖርም ” ሲሉ ትራምፕ ገልጸዋል።

” ከእንግዲህ በኋላ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አይኖራቸውም። በዚያ ይስማማሉ። ያለዚያ ግን ስምምነት አይኖርም ” ብለዋል።

ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ የነዳጅ ዋጋ በፍጥነት ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመው ነገር ግን አሁንም ለስምምነቱ ሙሉ ዋስትና እንዳልሌለና ሁኔታዎች ካልተሳኩ ጥቃቱ እንደሚቀጥል አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ንግግር መጀመሩን ቢናገሩም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተለያዩ የሀገሪቱ የዜና ወኪሎች (ፋርስ እና ታስኒምን ጨምሮ) መረጃውን ሙሉ በሙሉ አስተባብለዋል።

ኢራን ከአሜሪካ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምንም ዓይነት ንግግር አለማድረጓን ገልጻለች።

የሆርሙዝ ሰርጥ አሁንም ” ጦርነት ለከፈቱብን ዝግ ነው ” ያሉ ሲሆን ” ትራምፕ የጊዜ ገደቡን ያራዘሙት የኢራን አጸፋዊ እርምጃ ስላስፈራቸው እንጂ በድርድር አይደለም ” ሲሉ የዜና ምንጮቹ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተጀመረ ንግግር እንዳለና አገራቸው ይህንን እንደምታውቀውና እንደምትደግፈው ገልጸዋል።

ስታርመር ማንኛውም ስምምነት በተለይ በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ ጠንካራ ገደቦችን ሊያካትት እንደሚገባ አሳስበዋል።

መረጃው ከቢቢሲ፣ ታስኒም፣ ፋርስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ነው የተሰበሰበው።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe