የአእምሮ ውቅሮች ምንድናቸው  ኢድ፣ ኢጎ እና ሱፐርኢጎ

Id፣ Ego፣ Superego!

እንደ ሲግመንድ ፍሮይድ ሳይኮአናላይሲስ ጽንሰሃሳብ የሰው ልጅ አእምሮ በሶስት መሰረታዊ መሰረቶች እንደተዋቀሩ ያስቀምጣል። እነዚህ ሦስቱ የአእምሮ አካላት ኢድ (id)፣ ኢጎ (Ego) እና ሱፐር-ኢጎ ( Super ego) ተብለው ሲጠሩ፥ ውስብስብ የሆነውን የሰዎች ባህሪ እና ማንነት የሚገነባው በነዚህ በሚኖረው መስተጋብር ይሆናል ።

እንደ ፍሮይድ ጽንሰ-ሀሳብ መሠረት የሰው ልጅ ስብዕና የተወሰኑ ክፍሎች በመሰረታዊ ፍላጎቶችዎ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ ግፊት ሲያደርጉ ሌሎች የስብዕና ክፍሎች ደግሞ እነዚህን ፍላጎቶች ወይም ምኞቶች ለመግታት እና ከእውነተኛ አለም ጋር ካለው ሁኔታ እንዲስማሙ በመሞገት ነው።

፩) Id (ደመ-ነፍስ)

ይህ የአእምሮ አካል በአብዛኛው የነገሮችን ግንዛቤ ሚዛናዊነት የሚጎድለው ሲሆን ቀጥታ ውስጣዊ ፍላጎትን ማሟላት እና ወቅታዊ ደስታ ፍለጋ ላይ ብቻ ትኩረቱን የሚያደርግ ክፍል ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ ንቁ ባልሆነው የአዕምሮ ክፍል የሚዘወርም ነው።

ኢድ (id) ሁሉንም ፍላጎቶች ወዲያውኑ ለማሟላት ከሚሠራው የሰውነት የመደሰት መርህ የሚመነጭ እና የሚፈልገውን ፍላጎትን ለማርካት የአእምሮ ምስል በመፍጠርና የመጀመሪያ ደረጃ (ስጋዊ) ስሜትን በመጠቀም የተፈጠረውን ውስጣዊ ውጥረትን ለመፍታት ይሞክራል ፡፡ ምንም እንኳን ሰዎች ውሎ አድሮ የኢድን (id) ደመ – ነፍሳዊ ፍላጎት መቆጣጠርን ቢማሩም፣ ይህ የባህሪይ አካል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ተመሳሳይ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል ፡፡

፨ ምግብ፣ ውኃ፣ ጤና፣ ሙቀት፣ ወሲብ…ወዘተ የስነ ሕይወታዊ ፍላጎቶች ማዕከል ነው።

፨ አብሮን የተወለደ በመሆኑ ምንግዜም ደስታን፣ እርካታን ይሻል።

፨ ጊዜና ሁኔታ ስለማይገዱት ተጨባጭ እውነታን አይለይም።

፨ ምክንያት፣ ግብረ ገብነት አይገዛውም።

፨ እንደ ራስ ወዳዱ ብላቴና ደስታውን ብቻ ያስቀድማል።

፨ ማመዛዘን የጎደለው በመሆኑ እውነታን ያማከለ አይደለም።

  • ••

፪) Ego (እውነታ መር)

ይህ የአእምሮ ውቅር ሶስት የአዕምሮ ክፍሎችን (ንቁ፣ ከፊል ንቁ እና ድብቁ የአእምሮ ክፍሎች) ተገናዝበው የሚሰሩበት ሲሆን ምክንያታዊነትና የተወሳሰበ አስተሳሰብ በቃላት በመግለጽ አስተባብሮ በንቁና በከፊል ንቁ ከሆነው የአእምሮ ክፍሎች ጋር የሚያገናዝብም ሲሆን ድብቁ የአእምሮ ክፍል ደግሞ በ ኢጎ ውስጥ የሚወከለው ራስን በመከላከልና ለሁሉም ነገር ምክንያት በመፈለግ ላይ የሚያተኩረው ቦታን ይይዛል።

ይህ የአእምሮ ክፍል ጠቅላዩን ሁሉንም የመቆጣጠር፣ የአስተሳሰብ፣ ከእውነተኛ አለም ጋር የመጋፈጥ፣ ምንክንያት የመፍጠር እንዲሁም ውስጣዊ ግፊትን የማዘግየት ሃላፊነትን የሚወጣ ዋናው ክፍልም ነው። ኢጎ ከ ኢድ የሚዳብር ሲሆን የኢድ ግፊቶች በእውነተኛው ዓለም ተቀባይነት ባለው መልኩ እንዲገለፁ ያደርጋል ፡፡

ኢጎ የሚሠራው በእውነተኛው መርህ ላይ በመመርኮዝ ነው። ስለዚህ የኢድ ፍላጎቶችን በተጨባጭና በነባራዊ እይታ ተገቢ በሆነ መንገድ ለማርካት ይጥራል ማለት ነው። በቀደመው የአእምሮ ክፍል በ ኢድ እና በእውነተኛው አለም ይፈጠሩ የነበሩ አለመግባባቶች በቀጣይ በኢድና በኢጎ መካከል ሊቀጥል ይችላል ።

፨ የፍላጎትና የእውነታ አስታራቂ ነው።

፨ ንቁ በመሆኑ ከእውነታ ጋር ነው የሚተዋወቀው።

፨ የላቀ ምቾት እንድንጎናፀፍ ድርጊያዎቹን በጊዜና በሁኔታ ያከናውናል።

፨ የሁልጊዜ ስራው ኢድን ማገልገል ነው።

  • ••

፫) Superego (የሞራል ቋት ወይም ሕሊና)

ሱፐር-ኢጎ ከወላጆችና ከማህበረሰብ የምናገኛቸው የተወሳሰበ ባህል፣ የሞራል ግዴታዎችን፣ በውስጣችን ከተቀመጡ የሥነ-ምግባር መርህና አመለካከቶችን አዋህዶ የሚይዝ የስብዕና ክፍል ሲሆን ውስብስብ በሆነ መልኩ የግለሰቡን ባህሪይ አስተሳሰብ እና ስሜትን ከሚጠበቅበት የማህበረሰብ ደንብ አኗኗር እና ባህሪይ ንጻሬ በመስጠት የተሻለው ውሳኔ የሚሰጥበትም የአእምሮ ውቅር ነው።

ለምሳሌ አንድ ግለሰብ መንገድ ላይ ሽንት ቢመጣበትና መሽናት እንዳለበት ቢሰማው የመጀመሪያው ነገር መንግድ ላይ ልሽናና ውስጣዊ ውጥረቴን ልቀንስ የሚል ሲሆን ሌላኛው የአእምሮ ክፍል ለዚህኛው ፍላጎት እውቅና ሰጥቶ ነገር ግን መንገድ ላይ መሽናት በማህበረሰቡ ዘንድ አስነዋሪ ተግባር መሆኑንና የሞራል ጥያቄ በማንሳት መሞገትና ተግባራዊ እንዳይሆን ምክንያታዊ ጉዳዮችን ያነሳል ማለት ነው።

በመሆኑም የተስተካከለ ማንነት በነዚህ የአእምሮ ክፍሎች በሚኖር መልካም መስተጋብር ላይ የሚመሰረት መሆኑን ይህ የሳይኮአናላይሲስ ሊቅ አስቀምጧል።

፨ ማህበረሰባዊ ሕግና ደንብ ይመራዋል። ሕጉ ከባህል፣ ከሃይማኖት፣ ከመንግስት የተቀዳ ሊሆን ይችላል።

፨ የሕብረተሰቡ ልማድ፣ ስነ-ምግባር፣ ግበረ ገብበት ይገዛዋል።

፨ ትክክልና ስህተት ያውቃል።

፨ ኢድና ኢጎ ግለሰብን ሲወክሉ ሱፐር ኢጎ ግን ኅብረተሰብን ይወክላል።

ሀ/ መጸዳዳት ብንፈልግ

በልጅነት Id ላይ ስለምንሆን በለበስነው ላይ ወይም ሰው እየተመለከተንም ቢሆን ሜዳ ላይ ባለማፈር ልናራግፍ እንችላል። ዋናው ፍላጎታችን ከውስጥ የታፈነውን ማቅለል እንጂ ስለምንም ነገር አይመለከተንም፣ አያገባንም።

Ego ሲመጣ እውነታውን ስለሚያውቅ ከሰው ተከልለን እንድናደርገው ይገፋፋናል።

Superego ግን የማህበረሰቡ ውጤት ስለሆነ በልጅነት የሽንት ቤት አጠቃቀምን (toilet training) አጣቅሶ በፖፖ (ሽንት ቤት መጠቀም ለማይችሉት ነው) ወይም ሽንት ቤት መጠቀም እንደሚገባን ያሳውቀናል።

ለ) የሰው ልጅ የሚላስ የሚቀመስ ከሌለው ወደ ሌብነትም ሊሄድ ይችላል።

Id የሚያስጨንቀው የርሃቡ ስሜት ስለሆነ ጊዜና ሁኔታ ሳይመርጥ እንዲሰርቅ ያስገድደዋል።

Ego ብልጥ ስለሆነ “ሰው በሚተኛበት ሰዓት በውድቅት ለሊት ይሻላል። ምክንያቱም ጨለማ ስለሆነ የመያዝ እድልህ ዝቅተኛ ነው። በተለይ ደግሞ ቢነቃብህ እንኳን በአንዱ ስርቻ ትደበቃለህ ወይም እብስ ብለህ ታመልጣለህ” ብሎ ለደህንነትህም ጭምር እንደሚያስብ ይቀደዳል። እስቡት ኢጎ ስህተት ስለመሆኑ ከመናገር ይልቅ የተሻለ ውጤት የሚያመጣውን መንገድ ይጠቁማል።

Superego ግን መስረቅ በህግ የተከለከለ ስለሆነ ያሳስርሃል። ይቅርብህ! ብትያዝ ደግሞ በማህበረሱ አስነዋሪ ተግባር ስለሆነ እራስህንም ቤተሰብህንም ታሰድባለህ፣ ታዋርዳለህ ይቅርብህ! ደግሞ ሌብነት ሀጥያት ስለሆነ በፈጣሪ ዘንድም ያስቀጣሃል ብሎ ሽብርና ፍርሃት ይለቅባሃል።

ሐ/ የጓደኛህ ወይም የወንድምህ ሚስት በጣም ውብ ነች። በተመለከትካት ቁጥር ወሲባዊ ስሜትህን ትቀሰቅሰዋለች። ከቅርብ ጊዜ በኋላ እሷም ፍላጎት እንዳላት ተረድተሃል። እናም በድንገት ቤታቸው ስትሄድ ጓደኛህ ወይም ወንድምህ ቤት የለም።

Id የወንድሙ ወይም የጓደኛው ቤት መሆኑን በመዘንጋት አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወሲባዊ ፍላጎቱን እዚሁ ለማርካት ይፈልጋል።

Ego ያለበትን ቤትና ሁኔታ ፈፅሞ አይዘነጋም። ሰው ሊመጣ ስለሚችል ሌላ የሚያስተማምን ድብቅ ቦታ ቢሆን የተሻለ ነው ይላል። ኢድና ኢጎ እጅና ጓንት ናቸው። በደንብ ይግባባሉ። ኢጎ ከኢድ አንፃር አልሸሹም ዞር አሉ አይነት ነው።

Superego “ዝሙት ሀፅያት ነው። በሰማይ ቤት ያስቀጣሃል። ለዛውም የወንድምህን ወይም የጓደኛህን ሃራም ነው። በጣም አስነዋሪና አጸያፊ ተግባር ነው። ይቅር ይበልህ ከየት አሰብከው?” ይልሃል።

ግን የሚያሳዝነው በአብዛኛው ሰው ዘንድ ሱፐር ኢጎ በኢጎና በኢድ ይሸነፋል። ትክክለኛ ውሳኔ መወሰን ካሻሽ ሱፐር ኢጎህን አድምጠው!

በመጨረሻ ወረታ (reward) ይኖርሃል። ሱፐር ኢጎህን ከሰማህ የሽልማት ወረታህን ኩራትና ክብር ታገኛለህ (ከራስህ)። ግን አልሰማ ብለህ ውጤቱ በመጥፎ ከተጠናቀቀ የቅጣት ወረታ ጥፋትና ፀፀት ያጎሳቁልሃል። ምናልባት Ego ድርጊቱ መጥፎ (መጀመሪያ ወይም መጨረሻ ላይ) መሆኑን ካወቀ Superego ለማሳመን ወይም የቅጣት ወረታህን ለመከላከል ስልተ-ምት (Defense Mechanism) ሊጠቀም ይችላል።

ማጣቀሻ፡-

Join: https://t.me/BookzHorizon

synopsis of psychiatry 11ኛ ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe