የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዳይቋጭ እና መላው አውሮፓም ከሩሲያ ወደ ጦርነት እንዲገባ ሙከራዎችን እያደረጉ ነው ሲሉ የሀንጋሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ መሪዎች እና የምዕራብ አውሮፓ ፖለቲከኞች በጥረት ላይ የሚገኘውን የሰላም ንግግር ማበላሸት ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ እነዚሁ መሪዎች አሁን መላው አውሮፓን ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ለማስገባት እየሰሩ ነው ብለው መግለጻቸውን ታስ ዘግቧል፡፡
ዲፕሎማቱ አክለውም ሀንጋሪ ከእንዲህ አይነቱ እንቅስቀሴ ተገድባ ትቆያለች ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሃንጋሪን የጦርነቱ ተሳታፊ ለማድረግ ሙከራዎች እንዳሉ ተናግረው፤እኛ ግን እንዲህ አይነቱን መንገድ ምርጫችን አናደርገውም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ዩክሬን ኔቶን የመቀላቀል እቅዷን ልትተወው ነው ተባለ፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የዩክሬንን ኔቶን የመቀላቀል ፍላጎት ለሰላም ሲባል ከዳር ሳያደርሱት ሊተውት እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ ዩክሬን አብዛታ ኔቶን መቀላቀል የምትፈልገው ዳግም ሊቃጣ ከሚችልባት የሩሲያ የወረራ ስጋት ራሷን ለመከላከል ነው፡፡ አሁን የተጀመረውን የሰላም ሂደት ወደ ውጤት ለማምራት ዩክሬን ፍላጎቷን ወደጎን ትላለች ማለታቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡
ዩክሬን አራት ዓመታት ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት ለመቋጨት ሲባል ስትዋጋለት የከረመችውን ጥያቄዋን ወደመተው ልትመጣ ነው ሲል ኤንቢሲ ነውስ አስነብቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ትላንት እሁድ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የደህንነት ዋስትና የሚሰጥ ከሆነ ኔቶን የመቀላቀሉን ጥያቄ ዩክሬን እንደምትተወው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
አስቀድሞ ግን ዩክሬን ኔቶን መቀላቀል እንደምትፈልግ ስትገልጽ ነበር የከረመችው፡፡ ከአሜሪካ፡ከአውሮፓ እና ከሌሎች ወዳጅ ሀገራት ካናዳ፡ጃፓን እና ሌሎችን ጨምሮ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጧት ዩክሬን የምትፈልገው ዳግም ሊፈጠር ከሚችል የሩሲያ ወረራ እንዲከላከሏት ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በተደጋጋሚ እየጠየቁ የሚገኙት ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላሁ የሚለውን ሃሳቧን እንድትሰርዘው እንዲሁም አሁን ይዛ ከምትገኘው 15 በመቶ ከሚሆነው የዶንባስ ክልል ለቃ እንድትወጣ ነው፡፡
ዶንባስ ምስራቃዊ የዩክሬን ክፍል ሲሆን ከጦርነቱ በፊት ሙሉ በሙሉ በዩክሬን ቁጥጥር ስር የነበረ ስፍራ ነው፡፡//

