የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት 60ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ተከበረ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ብቁ የሕግ ባለሙያዎችን በማፍራት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ብቁ የሕግ ባለሙያዎችን በማፍራት የአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ለማጠናከር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት 60ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሕግ ትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በአገሪቱ ላሉ የሕግ ትምህርት ቤቶች መሰረት ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ለፍርድ ቤቶች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራትና ለተለያዩ አካላት ተከታታይነት ያለው ሥልጠና በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፤ ትምህርት ቤቱ በአገሪቱ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ብቃት ያላቸው ዳኞችን፣ ጠበቃዎችንና ዓቃቤ ሕጎችን በማፍራት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በቀጣይም ትምህርት ቤቱ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ክፍተቶችን በማረምና የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ብቁ ባለሙያዎች የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተቀዳጀበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የሕግ ትምህርት ቤቱ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ካለው ቁርጠኝነት አንፃር የዩኒቨርስቲው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማግኘት እድገቱን ለማፋጠን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።
በመርኃ ግብሩ የቀድሞ ተማሪዎች መገኘት የትምህርት ቤቱን የስድስት አስርተ ዓመታት ጉዞ በግልፅ ለመገምገምና የተመራቂዎችን ትልቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ይሆናል ነው ያሉት። (ኢዜአ)፦

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe