የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ገለጸ

ከሰኔ 2014-ሰኔ 2015 ድረስ ያለዉን ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገዉ ኮሚሽኑ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢነቱ መቀጠሉን አስታዉቋል፡፡

ዓመታዊ ሪፖርቱ ካለፈው ዓመት አንጻር ግጭቶችን በሰላም በመፍታት ረገድ አበረታች ጅማሮዎች ቢስተዋሉም፣ በሪፖርት ዘመኑ ተለዋዋጭ እና ዘርፈ ብዙ የመብቶች ጥሰቶች በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት መፈጸማቸውን አብራርቷል።

የዘፈቀደ እስርና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም፣ በሚዲያና ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀሰ መብት ላይ የተጣለ የዘፈቀደ ገደብ፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ፣ በግዳጅ ማስነሳትና በኑሮ ውድነት የተነሳ የደረሰው እንግልትና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም አሳሳቢነታቸው ከቀጠሉ ጉዳዮች ውስጥ እንደሚገኙ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. የተጀመረው የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት እንቅስቅሴ ተከትሎ፣ በተለይም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እና የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር፣ በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣት፣ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘታቸው በተደጋጋሚ በሚያገረሹ ግጭቶች ሳቢያ የሚደርሰው ሞት፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የመሠረተ ልማቶች እና የንብረት ውድመቶች አሁንም አሳሳቢነቱ መቀጠሉን በሪፖርቱ አስታዉቋል፡፡

የዘፈቀደ እና ሕገ ወጥ እስሮች፣ አስገድዶ መሰወር፣ የዋስ መብትን አለማክበር፣ ድብደባና የማሰቃየት ድርጊቶች መፈጻመቸው ተጠቁሟል፡፡

በጦርነት እና በትጥቅ ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም፣ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አስፈላጊነት በተጨማሪ፣ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣት በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ላይም ከፍተኛ ጫና እና ጥሰት ማስከተሉን አንስቷል፡፡

እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ መሠረታዊ በሆኑ የምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚታየው ዋጋ መናር እና በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሰዎችን ለከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረጉ መሆኑ ኮሚሽኑ አሳሳቢ ጉዳዮች ብሎ ካመላከታቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. በተደረገው ዘላቂ ተኩስ ማቆም እና የሰላም ስምምነት መሠረት ማብቃቱና፤ ኮሚሽኑና የተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጣምራ ባካሄዱት ምርመራ ከሰጧቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል አንዱ የሆነውን የሽግግር ፍትሕ የሰላም ስምምነቱ አካል እንዲሆን መደረጉ፣ ይህንንም ተከትሎ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ የፖሊሲ አማራጮች (Green Paper) ማዘጋጀቱ እና ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች ማካሄድ መጀመሩ በመልካም ከተጠቀሱ እመርታዎች መካከል ናቸዉ፡፡

በስተመጨረሻም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በ2015 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ሰዎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ እና የመሥራት መብቶቻቸው ባልተከበረበት ሁኔታ የተመዘገቡ መልካም ለውጦች ዘላቂነት አይኖራቸውም” ያሉ ሲሆን፤ የትጥቅ ግጭቶችን ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ ለማስቆም እና የሰዎችን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ መከናወን ካለባቸው ተግባራት በተጨማሪ የፍትሕ እና የአስፈጻሚ አካላት ተቋማት በቁርጠኝነት የሕግ የበላይነትን ሊያስከብሩ” እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe