የኢትዮጽያ አየር መንገድ በአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ ከመኖሪያ ቦታቸው ለሚነሱ ሰዎች ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ሊያደርግ ነው ተባለ፡፡
አየር መንገዱ በቢሾፍቱ ከተማ በመጭው ዓመት ለሚያስገነባው አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ከቢሾፍቱ ከተማ ቦታውን መረከቡን እና ከቦታው የሚነሱ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል፡፡ ከቦታው የሚነሱ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈርም ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ለነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤት መገንባትን ጨምሮ ሂወታቸውን በዘላቂነት የሚመሩበትን ስራ አየር መንገዱ እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡
በቦሌ ኤርፖርት ላይ በተለያዩ ጊዚያት የማስፋፊያ ስራዎች ቢሰሩም አቅሙ በዓመት ከ25 ሚሊየን በላይ መንገደኞች በላይ ሊሆን አልቻለም ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡
የቦሌ አየር ማረፊያ መሀል ከተማ ላይ ያለ በመሆኑ ለማስፋፊያ ቦታ ስለሌለ በሌላ ቦታ ላይ ተጨማሪ ኤር ፖርት ማስፈለጉ በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ ቢሾፍቱ ከተማ ላይ አመቺ ቦታ ተገኝቶ አየር መንገዱ ቦታውን መረከቡን ገልጻል፡፡ ግንባታውም በመጭው ዓመት ህዳር/ታህሳስ ላይ ይጀመራል ተብሎ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ኤርፖርት በሁለት ደረጃ ይገነባል የተባለ ሲሆን፤የመጀመሪያው ደረጃ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን በዓመት ያስተናግዳል፡፡

