የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎች የድህረ-ሽያጭ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድድ መመሪያ ጸደቀ
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች ከእጅ በእጅ ሽያጭ በተጨማሪ የድህረ-ሽያጭ አገልግሎትም እንዲሰጡ የሚያስገድድ መመሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋሉን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስ፡ በተያዘው በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረገው መመሪያ አስመጪዎች ተሽከርካሪዎችን አምጥቶ በመሸጥ ላይ ብቻ የነበራቸውን የተለመደ አሠራር የሚቀይር ነው።” ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
አዲሱ መመሪያ አስመጪዎች ለገበያ ለሚያቀርቧቸው ምርቶች ሙሉ ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚያስገድድ እንደሆነም አማካሪው ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ መመሪያውን ለመተግበር ሦስት መሠረታዊ መመዘኛዎችን ያስቀመጠ ሲሆን አስመጪዎች ለሚያስገቧቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በቂ የመለዋወጫ ዕቃዎችን እንዲያቀርቡ ግዴታ እንደሚጥል ተገልጿል።
በተጨማሪም ተሽከርካሪዎቹ የሚጠገኑባቸው ደረጃቸውን የጠበቁ የጥገና ማዕከላት እና የሰለጠኑ የቴክኒክ ባለሙያዎች መኖር ከግዴታዎቹ መካከል ይገኙበታል።
ማንኛውም አስመጪ ለሚያስገባቸው ተሽከርካሪዎች ባትሪ ቢያንስ የ5 ዓመት ዋስትና መስጠት እንደሚጠበቅበትም አቶ አሰፋ በዝርዝር አስረድተዋል።
አሠራሩ ተጠቃሚዎች በመለዋወጫ እና በጥገና ባለሙያዎች እጥረት ምክንያት የሚገጥማቸውን ኪሳራ እና እንግልት ለማስቀረት ታስቦ የወጣ መሆኑ ተገልጿል።
በተያያዘም በዘርፉ ያለውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት መንግሥት ከውጭ ሀገራት በተለይም ከቻይና ጋር በመተባበር የቴክኖሎጂ ሽግግርና ሰፊ የሥልጠና ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ተብሏል።
አዲሱ መመሪያ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ተከትሎ የሚመጡ የጥገናና የአገልግሎት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

