የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ተቀጥረው እንዲሰሩ የሚፈቅድ ረቂቅ ደንብ ለፓርላማው ቀረበ

ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተደርጎ በአዲስ መልኩ በአዋጅ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቀጥሮ የሚያሰራቸውን ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ለማስተዳደር የሚያስችልው ረቂቅ ደንብ ለፖርላማው ቀረበ፤

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ የተመራው የኢቢሲ ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ደንብ  70 አንቀፆችን የያዘ ሲሆን ረቂቁ በፖርላማ አባላት በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፤

በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የሠራተኞች አዲስ ምደባ ሳቢያ ከ100 በላይ ሠራተኞችን  በማሰናበቱ በፍርድ ቤት ክስ የቀረበበት ኢቢሲ በአዲሱ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ውስጥ የሰራተኞችን ቅጥር ስንብትና ዝውውርን የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል፤

በአዲሱ የኢቢሲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1278/15 ጋር ለማጣጣም በሚል የወጣው ረቂቅ የሠራተኞች ደንብ  ድርጅቱ የውጭ ሀገር ዜጎችን ቀጥሮ ማሰራት እንደሚችል የሚደነግግ ሲሆን በተለይ ከሀገር ደህንነት ጥበቃ አንፃር ደንቡ ጥያቄ ተነስቶበታል፤

ከሀገር ደህንነት አንጻር የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገር መከላካያ ሠራዊት፤በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው እንዳይሰሩ ክልክል ሲሆን ፖርላማው በሀገሪቱ ትልቁ ብሔራዊ ጣቢያ ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጎች ተቀጥረው እንዲሰሩ የሚፈቅድ ረቂቅ ደንብ ማቅረቡ አነጋጋሪ ሆኗል፤በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በሶስቱ ተቋማት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ኤርትራውያን ‹ለሀገር ደህንነት አስጊ ናቸው› በማለት በአስቸኳይ ከስራ መሰናበታቸው የሚታወስ ነው፤

ማንኛውም ሠራተኛ በኢቢሲ ሲቀጠር ቃለ ማሕላ እንዲፈፅም የሚጠይቀው ረቂቅ ደንቡ ሠራተኞች ሕገ መንግስቱንና የመንግስትን ፖሊሲዎች መቃወም እንደማይችሉ ይደነግጋል፤ በደንቡ አንቀፅ አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀጽ 3/ላይ የቀረበው ቃለ ማህላ ‹እኔ … ህገመንግስቱን እንዲሁም የመንግስትን ፖሊሲዎች ማክበርና በህግ ወይም በአሰራር ስራ አጋጣሚ በእጄ የገባውን ሚስጥር ለማንኛውም ወገን ላለመግፅ ቃል እገባለሁ › ብለው እንዲፈርሙ ይገደዳሉ፤  ረቂቅ ደንቡ የኢቢሲን የአስተዳደር ሠራተኞችና ጋዜጠኞች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስቀመጡ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን ጋዜጠኞች በሙያቸው ከማንኛውም ወገን ነፃና ገለልተኛ ሆነው መረጃዎችን ለህዝብ እንዲያቀርቡ ያላቸውን የሙያ ነፃነት ይጋፋል በሚል ተተችቷል፤

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe