የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ብሔራዊ ባንክ በየ2 ሳምንቱ በሚያወጣው የዶላር ጨረታ ላይ ለመሳታፍ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡
ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በዚህ ዓመት ወደ ስራ የገቡት የውጭ ምንዛሬ ሱቆች በጨረታው ላይ ተሳታፊ መሆን እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ሲሰማ፤ብሔራዊ ባንክ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጽያ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ውስደው በስራ ላይ ያሉ የውጭ ምንዛሬ ሱቆች 12 ደርሰዋል፡፡
እነዚሁ ሱቆችም የብላክ ማርኬቱን በማዳከም የውጭ ምንዛሬ ህጋዊ ወደሆነ መንገድ እንዲገባ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ እንደ አብነትም በጥር ወር ላይ በህጋዊ እና ጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫ ዋጋ ልዩነት እስከ አንድ ብር ጠቦ እንደነበርም ተገልጻል፡፡
በዚህ ስዓት ግን ልዩነቱ ወደ አምስት ብር ከፍ እንዳለ ነው የተሰማው፡፡ በገበያው ውስጥ የራሳችን ሚና አለን፡ከአገር ውጭ ለሚጓዙ መንገደኞች የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ህዝብ እያገለገልን ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለብን በብሔራዊ ባንክ ጨረታ ላይ እንድሳተፍ ቢደረግ ስራችንን እንዲነቃቃ ያደርገዋል ማለታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
የኢትዮጽያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የውጭ ምንዛሪ ድርጅቶች በምንዛሬ ጨረታ ላይ እንዲወዳደሩ የሚፈቅድ አሠራር እንደሌለ ተናግሯል፡፡
እነዚሁ የምንዛሬ ቢሮዎች ብሔራዊ ባንክ በሚያዘጋጀው የምንዛሪ ጨረታ ከንግድ ባንኮች ጋር እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ፖሊሲ አለመኖሩንም ገልጻል፡፡
ድርጅቶቹ ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ ምንዛሬ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲሸጡ እንጂ ከባንኮች ጋር በጨረታ እንዲሳተፉ አይፈቀድም ነው ያለው፡፡
በራሳቸው በውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መካከል ያለው ውድድር ጤናማ የማይመስል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመካከላቸው ባለ ውድድር እስከ አስር ብር ድረስ ልዩነት ኖሮ እንደሚያውቅም ተሰምቷል፡፡ በርግጥ ገበያው በውድድር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ማንኛውም ተቋም በፈለገውና ያወጣኛል በሚለው ዋጋ መሸጥና መግዛት እንዲችል የሚፈቅድ ቢሆንም በመካከላችን ያለውን ውድድር ጤናማ እንዳይሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በሰሞንኛ ምንዛሬ ዋጋ አንድ ዶላር በአማካኝ ከ146 እስከ 150 ብር በመግዛት ላይ እንደሆኑም ታውቋል፡፡
በ155 ብር ደግሞ ይሸጣሉ፡፡ በጥቁር ገበያ ደግሞ አንድ ዶላር ከ156 ብር ባለይ እየተገዛ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የንግድ ባንኮች አንዱን ዶላር ከ124 ጀምሮ እስከ 133 ብር ድረስ በመግዛት ላይ ሲሆኑ የመሸጫ ዋጋቸው ደግሞ ከ126 እስከ 135 ብር ድረስ ነው፡፡

