ወንድዬ ዓሊ በ1950 ዓ.ም (እኤአ 1957) በቀድሞው የወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ ወረኢሉ አውራጃ ካቤ በምትባል መንደር ታክል ከተማ ተወለደ፡፡ ለወላጆቹ አምስተኛ ልጅ የሆነው ወንድዬ በእናቱ ፍቅር ተምበሽብሾ፣ ወደ ጫና በሚያደላው በአባቱ ጥብቅ ሥነ– ምግባር ተኮትኩቶ አደገ፡፡
ግጥም መግጠም የጀመረው ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ነበር፡፡‹‹የእናትና አባቴ ትዳር ከፈረሰ በኋላ አባቴ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ የእንጀራ እናቴ – በራሷ “ክፉ ቀን! ክፉ ሰው!” ሆነችብኝ፡፡ ፊቷ በገረፈኝ ቁጥር ቁጭቴን የምወጣው ወረቀት ላይ ነበር፡፡ አምስተኛ ክፍል ስደርስ እንጉርጉሮዎቼ አንድ ደብተር ሞሉ፡፡ ጥራዟን “ሲከፉ” የሚል ርእስ አወጣሁላት›› ይላል ወንድዬ አጀማመሩን ሲያስታውስ፡፡
ግጥሞቹ ግን ከባድማ ልቡ ብቻ የወጡ አልነበሩም፤ ከማንበብና መጻፍ በስተቀር ምንም ዘመናዊ ትምህርት ያልቀሰሙት አባቱ ለሕክምናም ሆነ ለፍርድ ቤት ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ባሉ ቁጥር ብርቅዬ ጫማ እና አልባሳት ሳይሆን መጻሕፍት ገዝተውለት ነበር የሚመጡት፡፡ ጦቢያ (የመጀመሪያው ልቦለድ በአፍሪቃ)፣ ወዳጄ ልቤ፣ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም፣ ፀሐይ መስፍን፣ እንቅልፍ ለምኔ ወዘተዎቹን. . . ያነበበው ካቤ መንደሩ ሳለ በኩራዝ ነው፡፡ የንባብ ፍቅር በዚያው ተጠናውቶት ቀረ፡፡
***
በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ በሚገኘው በታዋቂው የወይዘሮ ስኅን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ደሴ ከተማ በ1965 ዓ.ም (1972 እኤአ) ሲሄድ እንጀራ እናቱ ከሚያደርሱበት ሃበሳ ተገላገለ፡፡ እንጉርጉሮ – ጎርጉሮ የመክተቡም ነገር አብሮ ቀጥ አለ፡፡
ኪነ–ጥበባዊው ደመ–ነፍሳዊ አደራ ግን እንደ ጪስ (ጢስ) መውጪያ ስንጥቅ አታጣምና መንፈሳዊ ግጥሞችን መጫጫር ጀመረ፡፡ በደብረ ዘይት የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በ1971 ዓ.ም (1978 እኤአ) ገበቶ የደብረ ዘይት መካነ ኢየሱስ ኳየር ሲቀላቀል አምሮቱን ተወጣ፤ 200 ግድም ዜማ–ግጥሞችን (Lyrics) ዘመረ፤ አዘመረ፡፡ ስለ ዜማ–ግጥም ሥራዎቹ ሲናገር እንዲህ ይላል፡–
‹‹እነሱ እኮ! … ግጥሞቼ ሳይሆኑ፣ የዐውደ ዕለት ማስታወሻዎቼ (Diary) ናቸው፤ ግጥሞቼ ደግሞ – ታሪኮቼ››፡፡
ከነፍሱ ጥሪ በተቃራኒ እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የገባው በጊዜው ከነበረው ቀይ ሽብር አደጋ ለመሰወር ያህል ብቻ እንደ ነበረ – ያስታውሷል፡፡
***
ከኮሌጅ ሲመረቅ በሐምሌ 1972 (1980 እኤአ) አርሲ ተመደበ፡፡ በእንስሳት ሐኪምነትና በእንስሳት እርባታ ማኔጀርነት ዘጠኝ ዓመት ተኩል በሠራባቸው ዓመታት እውነተኛ ገጣሚነቱ ተፍለቀለቀ፡፡ በ1984 ዓ.ም (እኤአ 1992) በታተመቺው የመጀመሪያ መድበሉ “ወፌ ቆመች” ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአርሲ ቆይታው ነበር፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ኮተቤ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ” ክፍል ለማስተማሪያነት ካሪኩለም ውስጥ ለመካተት የበቃቺው “ወፌ ቆመች” እንግዲህ የእንስሳት ሐኪሙ – የቅኔ ዛር ምጥ ናት ማለት ነው፡፡
የወፌ ቆመች መታተም እና ዝና ኋላ ላይ ፍቅሩም፣ እንጀራውም ወደ ሆነው የሥነ ጽሑፍ ሙያ ይቀላቀል ዘንድ መንገድ ጠረገለት፡፡ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት የሥነ ጽሑፍ ድርጅት ባልደረባ ይሆን ዘንድ ጋበዘው፡፡ (በዚህ ረገድ የአቶ ጌታቸው በለጠ ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ ግብርና ምኒስቴርን ለቆ (ሞፈሩን ሰቅሎ፣ ቀምበሩን ሰብሮ) በትንሽ ደመወዝ በረዳት መጽሔት አዘጋጅነት ተቀጠረ፡፡
‹‹መጽሔት፡– እንደ ‹ቡፌ› ገበታ የተለያዩ መልእክቶች፣ በተለያዩ አቀራረቦች፣ በተለያዩ የአቀራረብ ቀለሞች፣ የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች መከሸን ይገባዋል፤›› ብሎ የሚያምነው
ወንድዬ የቃለ ሕይወትን መጽሔት እንደ ልቡ ናኘባት፡፡ እያንዳንዷን ቅጽ፡– የመጣጥፍ፣ የታዋቂ ሰዎች ፕሮፋይል፣ የቃለ ምልልስ፣ የግጥሞች . . . ገበታ አደረጋት፡፡ (እንዳሰኘው ይጽፍ ዘንድ ሙሉ ነፃነት ያጎናጸፉትን የቅርብ አለቆቹን ያመሰግናል)፡፡
በዚህ ወቅት ነበር ከሥነ ግጥም በተጨማሪ በሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች ለመጻፍ ተሰጥዖ እንዳለው ራሱን ያሳመነው፡፡ በተለይም በታሪክ እና የሕይወት ታሪኮች አተራረክ ረገድ ብዙ እርምጃ ተራመደ፡፡
ለዚህም ነበር፣ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንን ከፊል ታሪክ የሚሸፍነውን (1920-1966 ዓ.ም) ለመጻፍ የቻለው፡፡
በሁለት ቅጽ የተዘጋጁት መጻሕፍት “በመከራ ያበበች” እና “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” ይሰኛሉ፡፡ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ1990 ዓ.ም እና 1992 ዓ.ም የታተሙ ናቸው፡፡ መጻሕፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የፕሮቴስታንት (ወንጌላውያን) ቤተ እምነት ታሪክ በመሆናቸው በርካታ የሥነ መለኮት ኮሌጆች ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ውስጥ ተካተቱለት፡፡
በዚህ ደስ የተሰኙት አለቆቹ Tear fund England ከሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ኬኒያ – ናይሮቢ በሚገኘው Daystar ዩኒቨርስቲ የትምህርት ዕድል አመቻቹለት፡፡
በ40 ዓመቱ ተመልሶ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በአራት ዓመት ቆይታ ለመጀመሪያ ድግሪ መርሐ ግብር የተላከው ወንድዬ፣ በሦስት ዓመት ቆይታ የማስተርስ ዲግሪውን ይዞ ተመለሰ፡፡ ይህ ለብዙዎች ታምር ያህል እውነት ነው፡፡ ጥያቄም ነው፡፡
‹‹ሰው እንዴት ከveterinary ዲፕሎማ ተነስቶ በሦስት ዓመት፣ ለዚያውም ለMature Students የሚሰጠውን መሸጋገሪያ ኮርስ (Bridging Course) ሳይወስድ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ለዚያውም በሦስት ዓመት ብቻ ሊያጠናቅቅ ይችላል?›› ይህን ዝርዝር ለመዘርዘር ውጥኔ አይፈቅድልኝም፡፡
የወንድዬን የአዕምሮ ጉልበትና ሥራዎቹን በደንብ የተረዱ ሰዎች ‹‹ይህን ሰው ለመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር “ማባከን ነው” በማለት ከዩኒቨርስቲው ጋር የተሟገቱ እንደ ነበሩ ወንድዬ ያስታውሳል፡፡ የአቶ ወርቁ ኃይለ ማርያምን ግትገታ (ውትወታ) ግን ከሁሉ የበለጠ ነበርና ወንድዬ ሁሌም ያስታውሰዋል፡፡
ወርቁን እና ወዳጆቹን አላሳፈራቸውም፡፡ የመመረቂያ ወረቀቱን፡, “THE CONTRIBUTION OF ORAL LITERATURE IN COMMUNICATING THE GOSPEL TO THE OMOTIC PEOPLE OF SOUTHERN ETHIOPIA: A CASE STUDY OF THE WOLIATE PIONEER EVANGELISTS” በሚል ርእስ ሠርቶ በ2003 (እኤአ) በማስተርስ ድግሪ ተመረቀ፡፡
(ተወዳጅ ሚዲያ)

