የዓሣ ዘይት በርካታ ዝርያ ካላቸው የዓሳ አይነቶች የሚመረት ሲሆን በተለይም ኢ.ፒ.ኤ (አይኮሰፓንቶኖይክ) እና ዲ.ኤች.ኤ (ዶኮሳሄክሳኖይክ) በሚባሉ ሁለት ጠቃሚ ኦሜጋ -3 ፋቲ አሲዶች የበለፀገ እንደሆነ የኢትዮ የጤና መረጃን ጨምሮ የተለያዩ የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የዓሳ ዘይት ጥቅም እና ተፈላጊነትም ከዚህ ከኦሜጋ -3 ፋቲ አሲድ ይዘት አኳያ እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን፣ ሰውነታችን የራሱ የሆነ ብዙ ኦሜጋ -3 ፋቲ አሲድ አያመነጭም።
ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ በርካታ የጤና ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ለቆዳ ጤንነት፡- ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ የቆዳን ጤንነት፣ እርጥበት እና የመለጠጥ ችሎታን ጠብቆ ለማቆየት ይረዳል። ይህም እንደ ኤክማ እና ፕረሲየስ ያሉ የቆዳ ህመሞችን በእጅጉ ይቀንሳል።
ለአይን ጤና፡- ዲ.ኤች.ኤ (DHA) ረቲና የሚባለው የዓይን ክፍል ዋነኛ መዋቅራዊ አካል በመሆኑ፣ የዓሳ ዘይትን መመገብ የዓይን ጤናን ሊጠብቅ እና ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ማኩላር ዲጀነሬሽን የተባለውን በሽታ ይቀንሳል።
ለልብ ጤና፡- ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ ትራይግሊሰርይድን እና የደም ግፊትን በመቀነስ በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ላይ አላስፈላጊ ክምችት እንዳይፈጠር ስለሚያደርግ የልብ ህመም እና የስትሮክ አደጋን ይቀንሳል።
ለአዕምሮ ጤና፡- ዲ.ኤች.ኤ (DHA) ለአንጎል እድገት እና ተግባር ወሳኝ ሲሆን፣ ኦሜጋ -3 ፋቲ አሲድ ደግሞ የእውቀት (ኮግኒቲቭ) ተግባርን፣ ማህደረ ትውስታን እና ስሜትን ለማሻሻል ይረዳል፤ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣን የግንዛቤ መቀነስ ችግርም ይከላከላል።
ለመገጣጠሚያ ጤና፡- የዓሳ ዘይት ሰፕሊመንት እንደ አርትራይተስ ካሉ ሁኔታዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡትን የመገጣጠሚያ ህመሞች እና መገተር (ለማጠፍ መቸገርን) ለመቀነስ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የመገጣጠሚያ ተግባራትን እና እንቅስቃሴን ለማሻሻል ይረዳል።
ለኢንፍላሜሽን መቀነስ፡- ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ ፀረ-ብግነት ባህሪያት ያሉት ሲሆን፣ ይህም በሰውነት ውስጥ ያለውን ኢንፍላሜሽን ለመቀነስ እና እንደ ሪህ እና ኢንፍላማቶሪ የአንጀት በሽታ ያሉ ችግሮችን ያስወግዳል።
ለድባቴ እና ጭንቀት፡- ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ ድባቴ እና ጭንቀትን ሊከላከል እና ሊያቃልል እንደሚችል የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ለእርግዝና እና ለጨቅላ ህጻናት እድገት፡- ዲ.ኤች.ኤ (DHA) በእርግዝና ወቅት ለፅንስ አንጎልና ለዓይን እድገት ወሳኝ ነው። የዓሳ ዘይት ሰፕሊመንትን መውሰድ ጤናማ የእርግዝና ሂደቶችን እና የህጻናት እድገት እንዲኖር ያስችላል።
የዓሳ ዘይት ብዙ የጤና ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም፣ በመጠኑ ወይም በልክ መጠቀም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከመጠን በላይ የዓሳ ዘይት መውሰድ፤ ከፍተኛ የደም መፍሰስ እና በሽታ የመከላከል አቅም መዛባት የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡
እንደ ማንኛውም ሰፕሊመንቶችን አዲስ ከመጀመር ወይም ከመውሰድ በፊት የጤና ባለሙያ ማማከር ተገቢነት እንዳለውም የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በኦሜጋ -3 የዓሣ ዘይት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች፣ በሌሎች ምግቦች ውስጥም እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ፡- ዓሣን ጨምሮ በባህር ምግቦች፣ በተለያዩ አትክልቶችና ጥራጥሬዎች ውስጥ እንደሚገኙ የተለያዩ የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

