(ይትባረክ ዋለልኝ)
የ80 ዓመት ወላጅ እናቱ በክብር እንግድነት ተግኝተው የሚወዱት ልጃቸውን መፅሐፍ በክብር መረቁ!
በጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ የተጻፈው “ዜሮ ዓመት የስራ ልምድና ሌሎች ወጎች” የተሰኘው መጽሐፍ ትላንት ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በግሮቭ ጋርደን ዎክ መርቀናል:: ይህንን መፅሐፍ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የሰማንያ ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት የታምራት ሃይሉ እናት ነበሩ:: ታምራት ዛሬ እርሱ እዚህ ለመድረስ የእናቱ አስተዋፅዖ እንደማይሰፈርና እንደማይለካ ስሜታዊ አድርጎት እንባ አሸንፎት በቃላት መግለፅ አቅቶት ነበር :: በታሜ ንግግር ታዳሚውንም እጅግ ስሜታዊ አድርጎታል:: ካጠገቤ የተቀመጠው ኮሜዲያን ደረጄም በታሜ ንግግር እንባ ሲተናነቀው ተመልክቻለሁ:: አርቲስት ፍቅርተ ጌታሁን ለታምራት እናት ኩታና ሙሉ የባህል ልብስ በስጦታነት አበርክታላቸዋለች::ይህንን “ዜሮ ዓመት የስራ ልምድና ሌሎች ወጎች” መፅሐፍም ከእናቱ በላይ ማንም ሌላ ሰው የክብር እንግዳ ሆኖ ሊመርቅ እንደማይችልም በምሳሌ ተናግሯል::

ይህ የትላንቱ የመፅሐፍ ምርቃት ፕሮግራም ታምራት እናት የተመሰገኑበት ቀን ነበር:: ታምራት ስለእናቱ ያለውን ፍቅርና አክብሮት የገለፀበት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን እናቱም ስለልጃቸው ያላቸውን ፍቅርና ማንነት ግሩም ምስክርነት የሰጡበትም ፕሮግራም ነው::

በዚህ የመፅሐፍ ምርቃት ፕሮግራሙ ላይ መፅሐፉ ታትሞ እውን እንዲሆን በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የመፅሐፍ ቅድመግዢ እንዲያደርጉ በማድረግ እውን እንዲሆን ያደረገው ደራሲና ጋዜጠኛ ቴወድሮስ ተ/አረጋይ እንደሆነ ታምራት ተናግሮ ከፍተኛ ምስጋናውን አቅርቧል:: ቴወድሮስ ተ/አረጋይም ዘመቻው እንደቀልድ ተጀምሮ እዚህ እንደደረሰና ብዙ ሰዎች እኔን አምነው ይህንን ዘመቻ በመቀላቀል መፅሐፉ ታትሞ ለዛሬው ቀን እንዲበቃ ላደረጉት ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል:: አያይዞም ብዙ ደጋግ ኢትዮጵያውያን አሉ ማህበራዊ ሚዲያውን ለመልካም ተግባር ብናውለው ብዙ ብዙ መልካም ተግባር እንከውንበታለን ብሏል ቴወድሮስ ተ/አረጋይ::
ታምራት ኃይሉም በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ቀድመው የገዙትን የሁሉንም ፎቶዎች በእስክሪን ላይ በማሳየት አመስግኗል:: መፅሐፉን ለገዙ ሁሉም ሰዎች ደግሞ የገዙትንም መፅሐፍ ፓኬጅ አሰርቶ በክብር ከመድረክ ላይ እንዲሰጣቸው አድርጏል:: በእለቱ ላልተገኙት ደግሞ በሐገር ውስጥም በውጭ ሐገርም ላሉ ኢትዮጵያውያን የገዙትን መፅሐፍ እንደሚያስረክብ ታምራት ተናግሯል::
በፕሮግራሙ ላይ አንጋፋው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴን ጨምሮ ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፣ ኮሜዲያን ደረጀ ሃይሌ፣ ጋዜጠኛ በላይ በቀለ፣ ገጣሚ ታገል ሰይፉ፣ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ፣ ገጣሚ ተስፋሁን ፀጋዬ፣ ጋዜጠኛ ኤደን ገ/ህይወትና ደራሲ በሃይሉ ገ/እግዚአብሔር ቅንጭብ ታሪኮችንና ገጠመኞቻቸውን አቅርበዋል::

