የጋዜጠኞችን ደህንነትና መብት የሚያስከብር የሚዲያ ጠበቆች ማህበር ተመሠረተ

(ቁም ነገር ሚዲያ፤ አዲሰ አበባ፤ መጋቢት 16፤2018)የጋዜጠኞችንና የመገናኛ ብዙኃን መብቶችን የሚያስከብርና በዘርፉ የሚታዩ የሕግ ጥሰቶች ላይ የሚያማክር የሚዲያ ጠበቆች ማህበር ተመስርቶ ስራ መጀመሩ ይፋ ሆነ፡፡

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች  ህብረት(ሴሮ) አስተባባሪነትና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እገዛ የተመሰረተው የሚዲያ ጠበቆች ማህበር ( The Lawyer’s for Media Association) በበጎ ፈቃድ ጠበቆችና ጋዜጠኞች ትብብር የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከሕግ አግባብ ውጪ የሚያዙ፤ የሚታሰሩና አድራሻቸው የማይታወቁ ጋዜጠኞችንና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን የህግ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን በፍርድ ቤት  የተመሰረቱ ክሶችንም ተከሳሾችን ወክሎ የሚቆም መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዘርፉ የሚታዩ የህግ ክፍተቶችና የአፈፃፀም ችግሮች ላይ የጥናትና የምርምር በማድረግ ለህግ አውጪዎችና ለፖሊሲ ነዳፊዎች ግብዓት የሚሆኑ ስራዎችን የመስራት ዓላማ ያለው የሚዲያ ጠበቆች ማህበር ከሁለት ዓመታት ውይይቶችና ምክክሮች በኋላ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ህጋዊ የምዝገባ ፈቃድ አግኝቶ መመዝገቡን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡

ቦርድ አባላት

በማህበሩ የምስረታ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ እውነቱ አለነ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር የጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ደህንነት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ሁሉም አካላት በትብብር የመስራት ባህልን ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትን ለመጠበቅ የወጡ በርካታ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ህጎቹን ወደ ተግባር በመተርጎም በኩል የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልፀው የጋዜጠኞችም ሆነ የሚዲያ ተቋማት መብቶች ሲጣሱ በህግ አግባብ ጥያቄዎችን የሚያቀርብና የሚከራከር የህግ ባለሙያዎችን ያካተተ ማህበር መመስረቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ የምክር ቤቱ አባል ሆኖ ህግ ነክ ጉዳዮችን በማማከር የፕሬስ ነፃነትን ለማስከበር በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በማህበሩ ምስረታ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የዬኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሪታ የንግግር ነፃነትና ሃሳብን በነፃነት የመግለጥ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ በዩኔስኮ እገዛ በኢትዮጵያ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የህግ ጥሰት ሲኖርና አላግባብ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት ጥቃት ሲደርስባቸው የጥብቅና አገልግሎት በበጎ ፈቃድ የሚሰጥ የባለሙያዎች ማህበር መመስረቱ የንግግር ነፃነትን ለማስከብር አንድ እርምጃ ይሆናል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኔስኮ እንደከዚህ ቀደሙ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በምስረታ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙ የጀርመን፤ የፈረንሳይ የስዊዲንና የእንግሊዝ ኤምባሲ ተወካዮችም የንግግር ነፃነት በኢትዮጵይ ስር እንዲሰድና ደህንነቱ የተጠበቀ የመገናኛ ብዙሃን ስራ እንዲኖር እንደወትሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe